በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የግሪክ ወንድሞቻችን በገለልተኝነታቸው የተነሳ ለግዞት ወይም ለእስር ይዳረጉ ነበር። ሆኖም በሚቻልበት ጊዜ ሁሉ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ማከናወናቸውን ቀጥለዋል፤ ለምሳሌ፣ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያን ያከብሩ ነበር

ታኅሣሥ 22, 2022
ግሪክ

ጦርነት አይማሩም—የመቶ ዓመት ታሪክ

ጦርነት አይማሩም—የመቶ ዓመት ታሪክ

ኒኮስ እና እሌኒ አባትዚስ

ግሪክ ለሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች 2022 ልዩ ትርጉም ያለው ዓመት ነው፤ ሁለት ወሳኝ ክንውኖችን ያስታውሳቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው በይፋ ሪፖርት የተደረገው የዛሬ 100 ዓመት ነው፤ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ከተዘረጋ ደግሞ 25 ዓመት አስቆጥሯል።

በ1900ዎቹ ዓመታት ግሪክ ብዙ ወታደራዊ ግጭቶች አስተናግዳለች። በዚህ የተነሳ ወንድሞቻችን ከገለልተኝነት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ችግሮች አጋጥመዋቸዋል። ግሪክ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነው ሕሊናቸው የተነሳ አቋም የወሰዱት የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች (ያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች) ወንድም ኒኮስ አባትዚስ እና ኒኮላዎስ ሬቤቦስ ናቸው።

ወንድም አባትዚስ ከ1919-1922 በተካሄደው የግሪክና የቱርክ ጦርነት ላይ ለመካፈል ፈቃደኛ አልሆነም። ወንድም አባትዚስ ያን ጊዜ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “[በትንሿ እስያ] ወደሚገኝ ጦር ሰፈር ተላክሁ . . . እዚያም ራሴን አደፋፍሬ [ለወታደሮቹ] መስበክ ጀመርኩ፤ ‘ጦርነት ከወንጌል ጋር ይጋጫል፤ ወንጌል የሚያዘን ጠላቶቻችንን እንድንወድ ነው’ አልኳቸው።” ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ወንድም አባትዚስ ግሪክ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ሰብኳል።

ኒኮላዎስ ሬቤቦስ እና ባለቤቱ

ኒኮላዎስ ሬቤቦስ በግሪክና በቱርክ ጦርነት ላይ ወታደር ነበር። ሆኖም ቅዱሳን መጻሕፍትንና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ያዘጋጁትን ትራክት ካነበበ በኋላ ለጦርነት ያለው አመለካከት ተቀየረ። ከዚህ በኋላ ጦርነት ውስጥ እንደማይገባ ለአዛዦቹ ነገራቸው፤ እርግጥ ይህ ውሳኔ የሞት ቅጣት ሊያስከትልበት እንደሚችል ያውቅ ነበር። ‘አምላክ ካልፈቀደ ግን ከፀጉሩ ላይ አንዷን እንኳ መንካት እንደማይችሉ’ በድፍረት ነገራቸው። ከጦርነቱ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ፈልጎ አገኛቸው፤ ከዚያም በ1925 ተጠመቀ።

ለመነሻ ያህል ወንድም አባትዚስን እና ሬቤቦስን ጠቀስን እንጂ የጦር መሣሪያ እንዲያነሱ ከፍተኛ ጫና ቢደረግባቸውም የገለልተኝነት አቋማቸውን የጠበቁ በርካታ የግሪክ ወንድሞቻችን አሉ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዲሁም ከ1946-1949 በተካሄደው የግሪክ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ ወንድሞቻችን ጦር ሠራዊቱንም ሆነ ዓማፅያኑን ለመቀላቀል ፈቃደኛ አልሆኑም፤ በዚህ የድፍረት አቋማቸው የተነሳ አንዳንዶቹ ተገድለዋል። ለስደት ከመንበርከክ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን የሰላም መልእክት ማወጃቸውን ቀጠሉ፤ በውጤቱም በ1940 178 የነበሩት የግሪክ የይሖዋ ምሥክሮች በ1949 ወደ 2,808 ደርሰዋል።

በዘመናችን የይሖዋ ምሥክሮች ግሪክ ውስጥ በቅንዓት ሲሰብኩ

ግሪክ፣ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑትን የይሖዋ ምሥክሮች ማሰሯን ቀጠለች። በድምሩ 3,788 ወንድሞች በገለልተኝነት አቋማቸው የተነሳ ታስረዋል። በመጨረሻም በ1997 ግሪክ አማራጭ የሲቪል አገልግሎትን በሕግ አጸደቀች። በአሁኑ ወቅት ግሪክ ውስጥ 100 ገደማ ወንድሞቻችን አማራጭ የሲቪል አገልግሎት እየሰጡ ነው።

በ2022 የአገልግሎት ዓመት ግሪክ 27,995 የደረሰ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር አስመዝግባለች፤ የተጠማቂዎች ብዛት ደግሞ 420 ነው።

ባለፈው ምዕተ ዓመት የግሪክ ወንድሞቻችን ጦርነትን ላለመማር ያሳዩትን ቆራጥነት ይሖዋ እንደባረከላቸው ግልጽ ነው።—ኢሳይያስ 2:4