ታኅሣሥ 23, 2019
ጓቴማላ
ለጓቴማላ ፖሊሶችና የእሳት አደጋ ሠራተኞች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወርክሾፕ ተዘጋጀ
ግንቦት 2019 የጓቴማላ ባለሥልጣናት ወንድሞቻችን ለእሳት አደጋ ሠራተኞችና ለፖሊሶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወርክሾፕ እንዲያዘጋጁ ፈቃድ ሰጡ። እስካሁን ድረስ 450 የእሳት አደጋ ሠራተኞችና ፖሊሶች በወርክሾፖቹ ላይ ተገኝተዋል፤ ወርክሾፖቹ የሚካሄዱት በኳቴፔኬ፣ በኮሎምባ ኮስታ ኩካ፣ በማላካታን እና በሳን ራፋኤል ፔትሳል ከተሞች ውስጥ ነው።
በወርክሾፖቹ ላይ የተካፈለ ሁዋን ካርሎስ ሮዳስ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ጓቴማላ ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በሦስት የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ላሉ እስረኞች ከ15 ለሚበልጡ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሲሰጡ ቆይተዋል። የእስር ቤቶቹ ኃላፊዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ እስረኞች የባሕርይ ለውጥ እንዳደረጉ አስተውለዋል። በዚህም ምክንያት ለፖሊሶችና ለእሳት አደጋ ሠራተኞችም ተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲሰጥ ሐሳብ አቀረቡ።”
በማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ አመራር ሥር የሚካሄዱት እነዚህ ወርክሾፖች በሳምንት ሁለት ጊዜ ለ15 ደቂቃ ያህል ይቀርባሉ። ወርክሾፖቹ ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖር፣ ሥልጣንን በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም በቡድን መሥራት የሚቻልበትን መንገድ ጨምሮ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳሉ። ወርክሾፖቹን የሚመሩት ወንድሞች ከትምህርቱ ጋር የሚያያዙ ጽሑፎችን ይሰጣሉ፣ ከድረ ገጻችን ላይ ቪዲዮዎችን ያሳያሉ እንዲሁም JW ላይብረሪ የተባለውን አፕሊኬሽን ተጠቅሞ መረጃ ማግኘት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ያሳያሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች ለፖሊሶችና ለእሳት አደጋ ሠራተኞች እነዚህን ወርክሾፖች ማዘጋጀት በመቻላቸው ደስተኞች ናቸው። ሠልጣኞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ጥቅም ማግኘታቸውን እንደሚቀጥሉ ተስፋ እናደርጋለን።—2 ጢሞቴዎስ 3:16