ሐምሌ 9, 2020
ጣሊያን
በጣሊያን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት በውትድርና የማይካፈሉ ሰዎች መብት እንዲከበር አስተዋጽኦ ያደረጉት እንዴት ነው?
ጣሊያን በዛሬው ጊዜ እንዳሉ በርካታ አገሮች፣ በእምነታቸው ምክንያት በውትድርና አገልግሎት የማይካፈሉ ዜጎቿን መብት ታከብራለች። ቀደም ባሉት ጊዜያት ግን ዜጎች እንዲህ ያለ መብት አልነበራቸውም። ጣሊያን ይህን መሠረታዊ የሆነ ሰብዓዊ መብት እንድታከብር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተው የይሖዋ ምሥክሮች የከፈሉት መሥዋዕትነት ነው።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ለበርካታ ዓመታት፣ የጣሊያን ሕግ ወጣት ወንዶች በወታደራዊ አገልግሎት እንዲካፈሉ ያስገድድ ነበር። ጦርነቱ እንዳበቃ ማለትም በ1946 በመላው አገሪቱ ውስጥ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች 120 ብቻ ነበሩ። ሆኖም ራሳቸውን ለይሖዋ የሚወስኑ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲሄድ በእምነታቸው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥርም እየጨመረ ሄደ። እነዚህ ወጣቶች ይህን ውሳኔ ያደረጉት ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ ስለመሆን፣ ከዓመፅ ስለመራቅና ሌሎችን ስለመውደድ የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ለመታዘዝ ብለው ነው።
የጣሊያን ቅርንጫፍ ቢሮ በቅርቡ ያደረገው መጠይቅ እንደሚያሳየው በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉ ቢያንስ 14,180 የሚያህሉ ወንድሞች ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ታስረው እንደነበር ገልጸዋል። እነዚህ ወንድሞች በድምሩ 9,732 ዓመታት በእስር አሳልፈዋል፤ አብዛኞቹ ወንድሞች የታሰሩት ከ1960ዎቹ መጨረሻ እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።
በቱሪን፣ ጣሊያን የሚኖሩ የፀረ ውትድርና እንቅስቃሴዎችን ታሪክ የሚያጠኑ ሰርጂዮ አልቤሳኖ የተባሉ ምሁር “ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከታሰሩ ወጣቶች መካከል አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት” የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ተናግረዋል። አክለውም እነዚህ ወጣት ወንዶች የወሰዱት ቁርጥ አቋም “ችግሩ በማኅበረሰቡ ዘንድ ትኩረት እንዲሰጠው አስተዋጽኦ አድርጓል” ብለዋል።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ጁሊዮ አንድሪዮቲ በ1960ዎቹ የጣሊያን መከላከያ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በወታደራዊ አገልግሎት የማይካፈሉበትን ምክንያት ለማወቅ ከታሰሩት መካከል አንዳንዶቹን በግለሰብ ደረጃ አነጋግረዋቸው ነበር። በኋላም እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ያላቸው ጠንካራ እምነትና በፖለቲካ ጉዳዮች ላለመግባት የያዙት ቁርጥ አቋም በጣም አስገርሞኝ ነበር፤ የወታደሮችን የደንብ ልብስ ለመልበስ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተበየነባቸውን ረጅም የእስር ጊዜ በጽናት የተቋቋሙት እንዲሁ በአጋጣሚ አይደለም።”
ዜጎች በወታደራዊ አገልግሎት ያለመካፈል መብታቸው እንዲከበር የሚያዝ ሕግ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው በ1972 ነው። የሚያሳዝነው ሕጉ በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ ሌላ ዓይነት የሲቪል አገልግሎትን የሚፈቅድ ቢሆንም ይህ አገልግሎትም ቢሆን በወታደራዊ ሥርዓት ሥር የሚከናወን ነበር፤ ወንድሞቻችን ደግሞ ይህን አማራጭ መቀበል አይችሉም።
በመጨረሻም ሐምሌ 8, 1998 የጣሊያን መንግሥት በወታደራዊ ሥርዓት ሥር ያልሆነ ሌላ የሲቪል አገልግሎትን የሚፈቅድ አዲስ ሕግ ያወጣ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ይህን አማራጭ መጠቀም ቻሉ። ነሐሴ 2004 ጣሊያን ወጣት ወንዶች ወታደራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስገድደው ሕግ ከጥር 2005 ጀምሮ ሙሉ በሙሉ እንዲሻር ወሰነች።
የይሖዋ ምሥክሮች በጣሊያን የሕግ ሥርዓት ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋጽኦ እውቅና ከሚሰጡት በርካታ ምሁራን መካከል በሮም ሳፒየንዛ ዩኒቨርሲቲ ጠበቃና የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ሰርጂዮ ላሪቻ ይገኙበታል። እንዲህ ብለዋል፦ “በጦር ሠራዊት ውስጥ የሚያገለግሉ ቀሳውስት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆን ‘ክርስቲያኖች እርስ በርስ እንዲዋደዱ ከተሰጣቸው ትእዛዝ ጋር ምንም እንደማይገናኝ፣ ይህ አቋም እናት አገርን ከማዋረድ ተለይቶ እንደማይታይና እንዲህ የሚያደርጉት ፈሪዎች ብቻ እንደሆኑ’ ይናገሩ ነበር፤ የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ ጊዜ የያዙት ቁርጥ አቋም ጣሊያን ውስጥ የሕጉን ሥርዓትና የማኅበረሰቡን አስተሳሰብ ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።”
ወንድሞቻችን የያዙት አቋም ተጽዕኖ ያሳደረው በጣሊያን የሕግ ሥርዓት ላይ ብቻ አይደለም። በርካታ የእስር ቤት ጠባቂዎች የይሖዋ ምሥክር እስረኞችን ምግባር ካዩ በኋላ እነሱ ራሳቸው የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ወስነዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆኑት ጁሴፔ ሴራ “እነዚያ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች የተዉት ምሳሌ . . . መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንድጀምር አነሳሳኝ” ብለዋል። በ1972 የይሖዋ ምሥክር ሆኑ። (ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።)
ላለፉት በርካታ ዓመታት፣ በጣሊያንም ሆነ በሌሎች አገሮች ያሉ ወንድሞቻችንና ቤተሰቦቻቸው “ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም” የሚለውን ትእዛዝ በቁም ነገር በመመልከት የተዉልንን ግሩም የድፍረት ምሳሌ ማሰብ በጣም የሚያበረታታ ነው።—ኢሳይያስ 2:4