በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መስከረም 26, 2019
ጣሊያን

በናዚዎችና በፋሽስቶች ጥቃት ለተፈጸመባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ጣሊያን ውስጥ መታሰቢያ ቆመላቸው

በናዚዎችና በፋሽስቶች ጥቃት ለተፈጸመባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ጣሊያን ውስጥ መታሰቢያ ቆመላቸው

ትሪዬስቴ ውስጥ በሪሲዬራ ዲ ሰን ሳባ የቆመው መታሰቢያ። በማጎሪያ ካምፖቹ ውስጥ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ሦስት ማዕዘን ቅርፅ የተለጠፈበት የደንብ ልብስ ይለብሱ ነበር

በናዚዎችና በፋሽስቶች ጥቃት የደረሰባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመዘከር የቆመው መታሰቢያ ግንቦት 10, 2019 የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የታሪክ ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ጎብኚዎች በተገኙበት ተመርቆ ተከፍቷል። ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው በሰሜን ምሥራቅ ጣሊያን፣ ትሪዬስቴ በሚገኘው በሪሲዬራ ዲ ሰን ሳባ ነው፤ የሩዝ ማቀነባበሪያ የነበረው ይህ ቦታ በኋላ ላይ የአስከሬን ማቃጠያ ያለው ብቸኛው የጣሊያን ማጎሪያ ካምፕ ሆኖ ነበር። ፕሮግራሙ በአካባቢውም ሆነ በአገሪቱ ያሉ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስቧል፤ ከእነዚህ መካከል በአገሪቱ ብዙ ተመልካች ካላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አንዱ የሆነው ካናሌ 5 ይገኝበታል።

በጣሊያን የይሖዋ ምሥክሮች ቃል አቀባይ የሆነው ክርስቲያን ዲ ብላሲዮ ፕሮግራሙን የከፈተው ስለ ታማኝነት የሚገልጽ ንግግር በማቅረብ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “በእምነታቸው ምክንያት በሦስተኛው ራይክ [በናዚ መንግሥት] ጥቃት የተፈጸመባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። በቡድን ደረጃ ነፃ የመውጣት አማራጭ የተሰጣቸውም እነሱ ብቻ ናቸው። ነፃ መውጣት ከፈለጉ የሚጠበቅባቸው፣ ክርስቲያናዊ እምነታቸውን መካድና ለመንግሥት ድጋፋቸውን መስጠት ብቻ ነበር። ይሁንና ለክርስቲያናዊ አቋማቸው በድፍረት የቆሙ ሲሆን ለአምላክ ታማኝ መሆናቸውንና ለሌሎች ፍቅር ማሳየታቸውን ቀጥለዋል።” ከዚያም ወንድም ዲ ብላሲዮ አንድ ቪዲዮ አሳየ፤ ቪዲዮው፣ እህት ኤማ ባወር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እሷና ቤተሰቧ የደረሰባቸውን ስደት ስትተርክ የሚያሳይ ቃለ መጠይቅ ነው። እህት ኤማ ባወር፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሞት ጋር ቢፋጠጡም እንኳ አቋማቸውን ለማላላት ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ተናግራለች። በፕሮግራሙ መደምደሚያ ላይ፣ የትሪዬስቴ ከንቲባ የሆኑት ሮቤርቶ ዲፒያትሳ ንግግር አቅርበዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ መታሰቢያ በመቆሙ በጣም ተደስቻለሁ። እንዲህ ያለ ጥቃት ዳግመኛ እንዳይደርስ ጠንክረን መሥራት አለብን።” ከዚያም መታሰቢያው በይፋ ተመርቆ ተከፈተ።

በርካታ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች፣ ይህ ፕሮግራም መዘጋጀቱ ስላለው ጠቀሜታ አስተያየት ሰጥተዋል። ለምሳሌ፣ የጣሊያን ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ፌዴሬሽን የቀድሞ ፕሬዚዳንት የሆኑት ጆርጂዮ ቡሻርድ እንዲህ ብለዋል፦ “ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት አንጻር ሲታይ የይሖዋ ምሥክሮችን ያህል የሕይወት መሥዋዕትነት የከፈለ የለም። . . . ሆኖም ያሳለፉት አስቸጋሪ ሁኔታ አጠናክሯቸዋል፤ የሦስተኛው ራይክ ርዕዮተ ዓለምን በቡድን ደረጃ የተቃወመ ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ታሪክ ይመሠክራል፤ በአምላክ ፊትም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ምሥክርነት እንደተሰጣቸው እናምናለን።” (ሌሎች ሰዎች የሰጡትን አስተያየት ለማንበብ ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።)

ሪሲዬራ ዲ ሰን ሳባ የተባለውን ታሪካዊ ስፍራ በየዓመቱ 120,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች እንደሚጎበኙት ይጠበቃል። እያንዳንዱ ጎብኚ፣ የናዚዎችና የፋሽስቶች ጥቃት ሰለባ ቢሆኑም እምነታቸውንና የፖለቲካ ገለልተኝነታቸውን የጠበቁትን በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ለመዘከር የቆመውን ይህን መታሰቢያ የመመልከት አጋጣሚ ያገኛል።—ራእይ 2:10