በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የሮም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት

የካቲት 7, 2020
ጣሊያን

ወላጆች ልጆቻቸው ያለደም ሕክምና እንዲያገኙ የመምረጥ መብት እንዳላቸው የሮም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አረጋገጠ

ወላጆች ልጆቻቸው ያለደም ሕክምና እንዲያገኙ የመምረጥ መብት እንዳላቸው የሮም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አረጋገጠ

ታኅሣሥ 17, 2019 የሮም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ የልጆች ጉዳይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ብይን የሚሽር ውሳኔ አድርጓል፤ የልጆች ጉዳይ ፍርድ ቤቱ አንዲት እህት ልጇ ደም እንዲሰጠው ባለመፍቀዷ ምክንያት የወላጅነት መብቷ እንዲነጠቅ በይኖ ነበር። ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ እህታችን ልጇን የማሳደግ መብት መልሳ እንድታገኝ ከማድረጉም ባለፈ ምንም የሠራችው ጥፋት እንደሌለ ገልጿል። ይህ ውሳኔ ሌሎች የይሖዋ ምሥክር ወላጆችም ልጆቻቸው ያለደም ሕክምና እንዲያገኙ በመምረጣቸው ምክንያት የወላጅነት መብታቸው እንዳይነጠቅ ያደርጋል።

ክሱ የተጀመረው አንዲት እህታችንና የአሥር ዓመት ልጇ የመኪና አደጋ ባጋጠማቸው ጊዜ ነበር። ልጁ ጉዳት ስለደረሰበት ወደ ሆስፒታል ተወሰደ። ከሦስት ቀን በኋላ ሐኪሞች ለልጁ ቀዶ ሕክምና እንዲደረግለት ወሰኑ። እህታችን ልጇ ቀዶ ሕክምናም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ሕክምናዎችን በሙሉ እንዲያገኝ ፈቀደች፤ ሆኖም ደም እንዲሰጠው እንደማትፈቅድ ገለጸች። ሕክምናው አጣዳፊ ባይሆንም እንኳ ሆስፒታሉ እህታችን በሃይማኖቷ ምክንያት ያደረገችው ውሳኔ የልጇን ሕይወት ሊያሳጣ እንደሚችል በመግለጽ ውሳኔዋ ውድቅ እንዲደረግ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለአቃቤ ሕጉ ላከ። አቃቤ ሕጉም እህታችን ለልጇ የሚበጀውን ነገር እንደከለከለች በመግለጽ የልጆች ጉዳይ ፍርድ ቤቱ የወላጅነት መብቷን እንዲነጥቃት ጥያቄ አቀረበ። የልጆች ጉዳይ ፍርድ ቤቱ እንዲህ ያለ ውሳኔ ለማድረግ ሕጉ ባይፈቅድለትም አቃቤ ሕጉን ደግፎ ብይን አስተላለፈ። በመሆኑም እህታችን ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቀረበች።

ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ እህታችን አሳቢና አፍቃሪ እናት መሆኗን ከገለጸ በኋላ “በሃይማኖቷ ምክንያት ልጇ ደም እንዲሰጠው አለመፍቀዷ የወላጅነት ኃላፊነቷን አልተወጣችም እንደማያስብላት” ተናገረ። ፍርድ ቤቱ ለእህታችን የወላጅነት መብቷን የመለሰላት ከመሆኑም ሌላ ይህን መብቷን መነጠቋ ሕገ ወጥ እንደነበር ገልጿል።

በባሪ ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖታዊ ሕግ ፕሮፌሰር የሆኑትና ቀደም ሲል በጣሊያን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሠሩ የነበሩት ኒኮላ ኮላያኒ እንዲህ ብለዋል፦ “ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ እስማማለሁ። ፍርድ ቤቶች የልጆች ጉዳይ ፍርድ ቤቱ ያደረገውን ዓይነት ብይን የሚያስተላልፉ መሆናቸው በጣም አሳዛኝ ነው። እውነተኛ ሃይማኖታዊ ነፃነት ማግኘት ለአብዛኛው ሰው በተለይ ደግሞ ለይሖዋ ምሥክሮች ከባድ የሆነ ይመስለኛል።”

በጣሊያን ቅርንጫፍ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዴስክ አስተባባሪ የሆነው ወንድም ክርስቲያን ዲ ብላሲዮ እንዲህ ብሏል፦ “የሮም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ሃይማኖታዊ አድልዎ የሚንጸባረቅበትን ውሳኔ ስለሻረ ደስ ብሎናል። የይሖዋ ምሥክሮች ለልጆቻቸው በጣም ያስባሉ፤ እንዲሁም ክርስቲያናዊ ሕሊናቸውን በሚያከብር መልኩ ጥሩ ሕክምና ለመስጠት ፈቃደኛ ለሆኑት በርካታ ሐኪሞች አመስጋኝ ናቸው።”

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለልጆቻቸው የሚሰጠውን ሕክምና በተመለከተ ውሳኔ የማድረግ መብታቸውን ያስከብራል። በተጨማሪም ውሳኔው የእምነት ባልንጀሮቻችን ከሕክምና ጋር በተያያዘ ከክርስቲያናዊ ሕሊናቸው ጋር የሚስማማ ምርጫ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል፤ በመሆኑም ይህን ድል ያስገኘልንን አምላካችንን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።—መዝሙር 37:28