በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድሞችና እህቶች በሮም በተካሄደው የቀዶ ሕክምና ሳይንሳዊ ማኅበራት አጠቃላይ ስብሰባ ላይ በደም ምትክ የሚሰጡ የሕክምና አማራጮችን በተመለከተ መረጃ ሲሰጡ

ሰኔ 27, 2019
ጣሊያን

ጣሊያን ውስጥ በተደረጉ ሁለት ትላልቅ የሕክምና ኮንፈረንሶች ላይ የተገኙ ሐኪሞች በደም ምትክ የሚሰጡ የሕክምና አማራጮች ያላቸውን ጠቀሜታ ገለጹ

ጣሊያን ውስጥ በተደረጉ ሁለት ትላልቅ የሕክምና ኮንፈረንሶች ላይ የተገኙ ሐኪሞች በደም ምትክ የሚሰጡ የሕክምና አማራጮች ያላቸውን ጠቀሜታ ገለጹ

የሕክምና ባለሙያዎች በፓሌርሞ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ የመረጃ ዴስካችንን ሲጎበኙ

ድርጅታችን በደም ምትክ የሚሰጡ የሕክምና እና የቀዶ ጥገና አማራጮችን በተመለከተ መረጃ ለመስጠት ላደረገው ዓለም አቀፋዊ ዝግጅት በርካታ ሐኪሞች አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በሮም በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ያለው የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት (ጣሊያን) የዚህ ዓለም አቀፍ ዝግጅት ክፍል ነው። ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት (ጣሊያን) ወኪሎች እና የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባላት ከጥቅምት 10 እስከ 13, 2018 በፓሌርሞ፣ ሲሲሊ በተካሄደው “የጣሊያን የሰመመን፣ የማስታገሻ፣ የአጣዳፊ ሕክምና እና ልዩ እንክብካቤ ማኅበር” (SIAARTI) ብሔራዊ ስብሰባ ላይ የመረጃ ዴስክ አዘጋጅተው ነበር። እነዚህ ወንድሞች ኮንፈረንሱ እንዳለቀ በሮም “ላ ኑቮላ” የስብሰባ ማዕከል በተካሄደው የቀዶ ሕክምና ሳይንሳዊ ማኅበራት አጠቃላይ ስብሰባ ላይም አውደ ርዕይ አቅርበዋል።

እንዲህ ያሉ ኮንፈረንሶች በደም ምትክ የሚሰጡ የሕክምና አማራጮችን በተመለከተ ለበርካታ የሕክምና ባለሙያዎች ወቅታዊ መረጃ ለመስጠት ጥሩ አጋጣሚ ይከፍታሉ። በፓሌርሞ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ 2,800 የሰመመን ባለሙያዎች ተገኝተው ነበር። በሮም የተካሄደው ኮንፈረንስ ደግሞ ጣሊያን ውስጥ ከተካሄዱት የቀዶ ሕክምና ኮንፈረንሶች በሙሉ ትልቁ ሲሆን 3,500 የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ተገኝተውበታል። ስመ ጥር ከሆኑ የተለያዩ የሕክምና ተቋማት የመጡ ልዑካንም በኮንፈረንሱ ላይ ተገኝተዋል። ከእነዚህ መካከል የሁሉም የጣሊያን የቀዶ ሕክምና ማኅበራት አባላት እንዲሁም ጣሊያን ከሚገኘው የአሜሪካ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ኮሌጅ የመጡ ሰዎች ይገኙበታል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ጨምሮ በርካታ ብሔራዊ ተቋማትም ይህን ዝግጅት ደግፈዋል።

በሲሲሊ ከሚገኘው የካታንያ ፖሊክሊኒኮ ሆስፒታል የመጡ ቪንሴንዞ ስኩደሪ የተባሉ የሰመመን ባለሙያ በፓሌርሞ ያዘጋጀነውን የመረጃ ዴስክ ጎብኝተው ነበር። እኚህ የሕክምና ባለሙያ ጥር 18, 2019 የደም ቧንቧ መቀደድ ላጋጠመው የይሖዋ ምሥክር አስቸኳይ ሕክምና መስጠት አስፈልጓቸው ነበር። ይህን ውስብስብ ሕክምና ያለደም ማከናወን ችለዋል። ዶክተር ስኩደሪ “በ2018 በተካሄደው ስብሰባ ላይ ያዘጋጃችሁት የመረጃ ዴስክ በጣም ጠቃሚ ነበር። የሰጣችሁን መረጃ በእጅጉ ረድቶኛል” ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ በጣሊያን የሚገኙ ከ5,000 የሚበልጡ ሐኪሞች አስተማማኝና ውጤታማ የሕክምናና የቀዶ ጥገና ዘዴዎችን በመጠቀም የይሖዋ ምሥክሮችን ያለደም ለማከም ተስማምተዋል። ጣሊያን ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ 16,000 የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ ሕክምና ያገኛሉ።