ኅዳር 16, 2020
ጣሊያን
የጣሊያን ቅርንጫፍ ቢሮን የማዛወሩ ሥራ የተለያዩ መሰናክሎች ቢያጋጥሙትም ተጠናክሮ ቀጥሏል
ከኢኮኖሚ እና ከጤና ጋር የተያያዙ መሰናክሎች ቢያጋጥሙም በጣሊያን የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ቦሎኛ ወደተባለች ከተማ የማዛወሩ ሥራ ቀጥሏል። መስከረም 5, 2020 ይህ ሥራ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የተሸጋገረ ሲሆን በዚህ ዕለት የመጀመሪያው የመኖሪያ ሕንፃ ግንባታ ተጠናቅቋል። አዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ በ2023 መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
አምስት ወንድሞችን ያቀፈው የግንባታ ፕሮጀክት ኮሚቴ ከአዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በበላይነት ይከታተላል። የዚህ መኖሪያ ሕንፃ ንድፍና ግንባታ ሥራ የተሰጠው ለሌላ ድርጅት ሲሆን ድርጅቱ ሥራውን የጀመረው መስከረም 2018 ነው።
በአገሪቱ የሚገኙ ብዙ ድርጅቶች በ2019 ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ደርሶባቸው ነበር። በዚህም ምክንያት የንድፍና የግንባታ ሥራውን እንዲያከናውን የተቀጠረው ድርጅት ሥራውን ለማቆምና አሠራሩን ለማስተካከል ተገዶ ነበር። ደስ የሚለው ግን በዚህ ወቅት ከመኖሪያ ሕንፃው ጋር የተያያዙ መሠረታዊ ሥራዎች ተጠናቀው ስለነበር ሥራው ለረጅም ጊዜ አልተቋረጠም።
በ2020 መባቻ ላይ ቦሎኛን ጨምሮ መላው የሰሜን ጣሊያን ግዛቶች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተመቱ። በመሆኑም የአካባቢውና የአገሪቱ ባለሥልጣናት በከተማዋ ውስጥ በርካታ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ትእዛዝ አስተላለፉ፤ ከእነዚህ መካከል የግንባታ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል። ሆኖም ከአንድ ወር በኋላ ባለሥልጣናቱ አንዳንድ ገደቦችን ያነሱ ሲሆን የጤና መርሆችንና ድርጅታችን ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የሚመራባቸውን የደህንነት ደንቦች ባገናዘበ መልኩ ሥራውን መቀጠል ተችሏል።
የግንባታ ፕሮጀክት ኮሚቴው አባል የሆነው ወንድም ፓውሎ ኮምፓራቶ እንዲህ ብሏል፦ “ስለተከናወነው ሥራ ይሖዋን በጣም እናመሰግናለን። የእሱ መንፈስ ባይረዳን ኖሮ ያጋጠሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት አንችልም ነበር።”
ግንባታውን የሚያከናውነው ድርጅት ሊቀ መንበር የሆኑት ክሪስቲና ዳላካሳ እንዲህ ብለዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ጣሊያን ውስጥ ካሉት ዋና ዋና ሕንፃዎቻቸው አንዱን እንድንገነባ ስለመረጡን ደስ ብሎናል። ከእነሱ ጋር በአንድነት እየሠራን ነው፤ ይህም በግንባታው ወቅት ያጋጠሙንን ችግሮች ለመወጣት አስችሎናል። የይሖዋ ምሥክሮች ለፕሮጀክቶቻቸው ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ፤ በተለይ ግንባታው ላይ የሚሠሩት ሰዎች ደህንነት በጣም ያሳስባቸዋል።” ሐሳባቸውን ሲደመድሙ እንዲህ ብለዋል፦ “ከሁሉ በላይ ግን፣ ሐቀኛና ታማኝ ከሆኑ ሰዎች ጋር መሥራት በመቻላችን ደስተኛ ነኝ። ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በተስፋፉበት በዚህ ጊዜ፣ እንዲህ ያሉ ሰዎች ማግኘት ያበረታታል።”
ይሖዋ ስሙ እንዲከበር የሚያደርገውን ይህን ፕሮጀክት መደገፉን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 127:1