በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

(በስተ ግራ) አንድ ቤተሰብ በጉባኤያቸው ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶችን ለማበረታታት የሚያጽናኑ ሐሳቦች የተጻፉባቸው ፖስተሮች ይዞ። (ከላይ በስተ ቀኝ) አንዲት አቅኚ እህት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ጥናት ስታስጠና። (ከታች በስተ ቀኝ) አንድ ቤተሰብ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የጉባኤ ስብሰባ ሲከታተል

ሚያዝያ 9, 2020
ጣሊያን

የጣሊያን ወንድሞችና እህቶች በወረርሽኙ መሃል መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀዋል

የጣሊያን ወንድሞችና እህቶች በወረርሽኙ መሃል መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀዋል

ጣሊያን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጣም ከተስፋፋባቸው አገሮች መካከል አንዷ ነች። የጣሊያን ቅርንጫፍ ቢሮ በበላይ አካሉ አመራር ሥር ለወንድሞችና ለእህቶች ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ እርዳታ በመስጠት ላይ ይገኛል።

በሰሜናዊ፣ በማዕከላዊና በደቡባዊ የጣሊያን ክፍሎች ያሉ ወንድሞቻችንን ፍላጎት ለማሟላት ሦስት የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል። የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ ከወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጋር በመነጋገር በወረርሽኙ የተጎዱት አስፋፊዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር በተመለከተ ወቅታዊ መረጃ ያገኛሉ፤ የወረዳ የበላይ ተመልካቾቹ ደግሞ መረጃውን የሚያገኙት ከጉባኤ ሽማግሌዎች ነው።

የጉባኤ ሽማግሌዎች ተጨባጭ እርዳታ ከመስጠት ባለፈ አስፋፊዎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ማከናወናቸውን እንዲቀጥሉ እየረዷቸው ነው። ወረርሽኙ መጀመሪያ ከተከሰተባቸው ከተሞች አንዷ በሆነችው በሚላን አቅራቢያ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም ቪሊያም ቦሴሊ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞችና እህቶች ከቤታቸው ባይወጡም ሁሉም እርስ በርስ አዘውትረው ይነጋገራሉ። በተጨማሪም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በስብሰባዎች ላይ በመገኘት እርስ በርስ ይበረታታሉ፤ እንዲሁም ሐሳብ ይሰጣሉ። አረጋውያን የሆኑ ወንድሞችና እህቶችም ጭምር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ከሚተላለፉት ስብሰባዎች በእጅጉ እየተጠቀሙ ነው። ጉባኤዎቹ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አንድነታቸው እንደተጠናከረ ይሰማኛል።”

የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ በርካታ ሰዎች የይሖዋ ምሥክር ከሆኑ ቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ስብሰባዎቻችንን እየተከታተሉ ነው። አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ስብሰባ መገኘት አይፈልግም ነበር። አሁን ግን ስብሰባው ራሱ ወደ እሱ መጥቷል። . . . እሱም ስብሰባዎቹን መከታተል ያስደስተዋል!”

ወንድሞችና እህቶች ምሥራቹን ለመስበክ ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት እህት በዕድሜ ለገፋች እህት ተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቼር) ለመውሰድ በመኪና እየሄደች ሳለ ኬላ ላይ ሦስት ፖሊሶች አስቆሟት። እህታችንም አንዲት አረጋዊት ሴት ለመርዳት እየሄደች እንደሆነ ከገለጸችላቸው በኋላ የጉዞ ፈቃዷን አሳየቻቸው። ከዚያም ለሁሉም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ይሰማሃል? እና መከራ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል? የሚሉትን ትራክቶች አበረከተችላቸው። ፖሊሶቹም ተቀበሏት። እህት ተሽከርካሪ ወንበሩን ሰጥታ ስትመለስ ፖሊሶቹ በድጋሚ አስቆሟት። ከዚያም እህትን አመሰገኗትና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው ተስፋ ተጨማሪ መረጃ እንድትሰጣቸው ጠየቋት። እንዲያውም ሁለት የሥራ ባልደረቦቻቸውን ጠርተው ውይይቱን እንዲያዳምጡ አደረጉ። እህትም jw.org​ን አሳየቻቸው። አንደኛው ፖሊስ “በጣም እናመሰግናለን የኔ እመቤት፤ ዛሬ በጣም አስደስተሽናል” አላት።

ወንድም ቦሴሊ እንዲህ ብሏል፦ “ሌሎችን የማበረታታትና የማጽናናት ኃላፊነት ቢኖረኝም ወንድሞች ያላቸውን መንፈሳዊ ጥንካሬና ጽናት በማየት እኔ ራሴ ተበረታትቻለሁ። ለይሖዋ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ሳስብ እንባዬ ይመጣል። ወንድሞቻችን ከይሖዋ ያገኘናቸው ውድ ስጦታዎች ናቸው፤ ያለእነሱ መኖር አንችልም!”

ወንድሞቻችን ብዙ ችግሮች ቢደርሱባቸውም በመንፈሳዊ ጠንካራ እንደሆኑና ‘በእነዚህ መከራዎች እንዳልተናወጡ’ በግልጽ ማየት ይቻላል።—1 ተሰሎንቄ 3:2, 3