በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሮም ውስጥ የጣሊያን ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚገኝበት ፓላስ ኦቭ ጀስቲስ የተባለው ሕንፃ

ጥቅምት 1, 2019
ጣሊያን

የጣሊያን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአሳዳጊ መብት ጋር በተያያዘ እኩል ሃይማኖታዊ ትምህርት የመስጠት መብትን ደገፈ

የጣሊያን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአሳዳጊ መብት ጋር በተያያዘ እኩል ሃይማኖታዊ ትምህርት የመስጠት መብትን ደገፈ

ነሐሴ 30, 2019 በሮም የሚገኘው የጣሊያን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአሳዳጊ መብት ጋር በተያያዘ ጉልህ ቦታ የሚሰጠው ውሳኔ አስተላልፏል። ይህ የጣሊያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ፣ የይሖዋ ምሥክር የሆነች አንዲት እናት ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጇን ሃይማኖታዊ ትምህርት የማስተማር መብቷን የሚደግፍ ነው።

ከእናቲቱ ተለይቶ የሚኖረውና የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው የልጁ አባት፣ ልጁ መማር ያለበት የእሱን ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ብቻ እንደሆነ በመግለጽ ተከራክሮ ነበር። ሁለት የበታች ፍርድ ቤቶች ለልጁ ሌላ ሃይማኖት ማስተማር “ግራ መጋባት” ሊፈጥርበት እንደሚችል በመግለጽ ለአባትየው ፈርደውለት ነበር። እነዚህ ፍርድ ቤቶች ያስተላለፉት ውሳኔ እናትየው ሃይማኖቷን ለልጇ የማስተማር መብቷን የሚጋፋ ነበር። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የበታች ፍርድ ቤቶቹን ውሳኔ የሻረ ከመሆኑም ሌላ ሁለቱም ወላጆች ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጃቸውን ስለ እምነታቸው የማስተማር እኩል መብት እንዳላቸው አረጋግጧል። በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ሁሉም ሃይማኖታዊ ቡድኖች “በሕግ ፊት እኩል እንደሆኑ” ጎላ አድርጎ የገለጸ ሲሆን የበታች ፍርድ ቤቶቹ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ “መድልዎ” እንደፈጸሙ በመግለጽ አውግዟቸዋል። በዚህ ውሳኔ መሠረት ለልጆች ሃይማኖታዊ ትምህርት ከመስጠት ጋር በተያያዘ በወላጆች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ማንኛውም ዳኛ ልጁ የሚማረውን ሃይማኖት የመወሰን መብት የለውም።

ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ይህ ብይን ወደፊት ጣሊያን ውስጥ ከአሳዳጊ መብት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጉዳዮች ጥሩ መሠረት እንደሚጥል ተስፋ እናደርጋለን። ይህ ውሳኔ፣ ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ ወላጆችን እንደሚጠቅም ምንም ጥርጥር የለውም።—ኤፌሶን 6:4