ሐምሌ 18, 2019
ጣሊያን
የጣሊያን ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮችን ሕክምና የመምረጥ መብት አስከበረ
ግንቦት 15, 2019 በጣሊያን ውስጥ የመጨረሻውን ሥልጣን የያዘው ፍርድ ቤት ይኸውም የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንድሞቻችን ከሕክምና ምርጫ ጋር በተያያዘ የፈለጉትን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳላቸው ገለጸ። ፍርድ ቤቱ አንድ ታካሚ ደም መውሰድ ካልፈለገ ይህን መብቱን የሚያስከብርለት የሕክምና ወኪል የመምረጥ መብት እንዳለው ተናግሯል። በተጨማሪ ፍርድ ቤቱ የጣሊያን ሕግ አንድ ሰው ባጋጠመው የጤና እክል የተነሳ ስለ አቋሙ ማስረዳት የማይችልበት ሁኔታ የሚፈጠር ቢሆን እንኳ የሕክምና ወኪል መሾም እንደሚችል አረጋግጧል።
ይህ ውሳኔ የተደረገው የጉባኤ ሽማግሌ የሆነው ወንድም ሉካ ካፔሊ ካጋጠመው የፍርድ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ነው። ወንድም ካፔሊ፣ በአንጎሉ ውስጥ ያሉ የደም ሥሮች ጤናማ ባለመሆናቸው ለ25 ዓመታት የዘለቀ የጤና እክል አጋጥሞታል። ሕመሙ ተደጋጋሚ ሕክምና የሚጠይቅ ከመሆኑም ሌላ አንዳንድ ጊዜ መናገር እንዳይችል ያግደዋል። ወንድም ካፔሊ ሕክምና ከመጀመሩ በፊት የሕክምና ሰነድ ሞልቶ ባለቤቱን ፍራንቼስካን የሕክምና ወኪሉ አደረጋት። ሆኖም አንድ ዳኛና የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ የወንድም ካፔሊ ባለቤት የሕክምና ጉዳዮች ወኪሉ እንዳትሆን ከለከሏት፤ በመሆኑም ወንድም ካፔሊ ያለፍላጎቱ ደም እንዳይሰጠው የሚያደርገውን ሕጋዊ ከለላ አጣ።
የካቲት 16, 2017 የወንድም ካፔሊ ጉዳይ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተመራ። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የበታቾቹ ፍርድ ቤቶች ታካሚዎች በገዛ ሰውነታቸው ላይ መብት እንዳላቸው የሚገልጹትን የጣሊያንን ሕገ መንግሥትና የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ስምምነት እንደጣሱ ገልጿል። የሚያስገርመው ፍርድ ቤቱ አንድ ሰው አንድን ሕክምና ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነው በሃይማኖታዊ አቋሙ ምክንያት ከሆነ መብቱ ይበልጥ ሊከበርለት እንደሚገባ ገልጿል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ይህ ብይን የጣሊያን ፍርድ ቤቶች ወንድሞቻችን ደም ላለመውሰድ ያደረጉትን ውሳኔ ይበልጥ እንዲያከብሩ የሚያስገድድ ነው።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያደረገው ውሳኔ በጣሊያን ያሉ ወንድሞቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናቸው የተነሳ ደም ላለመውሰድ ያላቸውን ቁርጥ አቋም የሚያስከብር በመሆኑ ሁላችንም ተደስተናል።—የሐዋርያት ሥራ 15:29