በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቦሎኛ፣ ጣሊያን ውስጥ በመታደስ ላይ ያለው ባለ ስምንት ፎቅ ሕንፃ

ጥቅምት 23, 2019
ጣሊያን

ጣሊያን ውስጥ እየተገነቡ ያሉት አዳዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች

ጣሊያን ውስጥ እየተገነቡ ያሉት አዳዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች

በአሁኑ ወቅት የትርጉም ክፍል የሚገኝበት በኢሞላ የሚገኘው ሕንፃ

የጣሊያን ቅርንጫፍ ቢሮ ከሮም ወደ ቦሎኛ እና ወደ ኢሞላ ሊዘዋወር ነው። ቦሎኛ ከሮም በስተ ሰሜን 370 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፣ ኢሞላ የምትገኘው ደግሞ ከቦሎኛ 48 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። በቦሎኛ በሚገኘውና ወደፊት ቅርንጫፍ ቢሮ ሆኖ በሚያገለግለው ባለ ስምንት ፎቅ ሕንፃ ላይ መጠነ ሰፊ የእድሳት ሥራ ተጀምሯል። ከ2018 ጀምሮ በትርጉም እና ከትርጉም ጋር ተያያዥ በሆኑ ሥራዎች ላይ የሚካፈሉ ከ60 የሚበልጡ ቤቴላውያን ኢሞላ በሚገኘው በቅርቡ የታደሰ ሕንፃ ውስጥ መሥራት ጀምረዋል።

ወደ ቦሎኛ ለሚዘዋወሩት ቤቴላውያን መኖሪያ ለማዘጋጀት ሲባል ባለ ስድስት ፎቅ የመኖሪያ ሕንፃ ለቢሮ ከሚያገለግለው ሕንፃ አንድ ተኩል ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እየተገነባ ነው፤ ሕንፃው ከምድር በታች ባለ ሦስት ፎቅ የመኪና ማቆሚያ አለው። በዚያው አካባቢ ተጨማሪ መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸው አይቀርም።

በግንባታ ላይ ያለው ባለ ስድስት ፎቅ የመኖሪያ ሕንፃ ሲጠናቀቅ የሚኖረው ገጽታ

የይሖዋ ምሥክሮች ለቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግለውን የመጀመሪያ ሕንፃ የገዙት ሮም ውስጥ በ1948 ነበር፤ በወቅቱ ወደዚያ የተዛወሩት ከሚላን ነው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ጣሊያን ውስጥ ትልቅ እድገት ታይቷል። በ1940ዎቹ አጋማሽ ላይ ጣሊያን ውስጥ የነበረው አስፋፊዎች ብዛት ከ200 በታች ነበር። በአሁኑ ጊዜ የአገሪቱ አስፋፊዎች ቁጥር ከ250,000 በላይ ሆኗል፤ ይህም በአውሮፓ ውስጥ በየትኛውም የቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ሥር ካለው የአስፋፊዎች ቁጥር ይበልጣል። በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ሥር ያሉ አስፋፊዎች ቁጥር በጨመረ መጠን ተጨማሪ ቤቴላውያንና አዳዲስ ሕንፃዎች ያስፈልጋሉ። በ2006 የጣሊያን ቅርንጫፍ ቢሮ በተለያዩ ቦታዎች የነበሩት ሕንፃዎች ቁጥር 99 ደርሶ ነበር። ቅርንጫፍ ቢሮው ወደ ቦሎኛ ሲዘዋወር ግን አምስት ሕንፃዎች ብቻ የሚኖሩት ሲሆን የቤቴል ቤተሰብ አባላት ቁጥርም ይቀንሳል።

ይሖዋ ይህን ፕሮጀክት እንዲባርከው እንዲሁም እነዚህ አዳዲስ ሕንፃዎች ተጠናቀው ‘አዝመራው በነጣበት’ በጣሊያን ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ሥራ ለመደገፍ እንዲውሉ እንጸልያለን።—ዮሐንስ 4:35