ግንቦት 26, 2020
ጣሊያን
ጣሊያን ውስጥ ከአንድ የድንገተኛ ክፍል ሐኪም ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ
ወንድም ጃንዶሜኒኮ ጉላ ጣሊያን ውስጥ በኮሞ አቅራቢያ ባለው በኤርባ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ውስጥ የሚሠራ ሐኪም ነው፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በወንድማችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮበታል። ያም ቢሆን ወንድማችን ያለው እምነት ውስጣዊ ሰላም አስገኝቶለታል፤ ይህም በተሻለ መንገድ ሌሎችን ለማጽናናት ረድቶታል። (2 ቆሮንቶስ 1:4) በጣሊያን ቅርንጫፍ ቢሮ ከሚገኘው የሕዝብ ግንኙነት ዴስክ ጋር በቅርቡ ያደረገው ቃለ ምልልስ ይህን የሚያሳይ ነው።
ከወንድም ጉላ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ ከዚህ በታች አጠር ተደርጎ ቀርቧል፤ መልእክቱ ግልጽ እንዲሆን ቃለ ምልልሱ ላይ ጥቂት ማስተካከያዎች ተደርገውበታል።
በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ምን አጋጥሞሃል?
ጃንዶሜኒኮ ጉላ፦ በምሠራበት ሆስፒታል ውስጥ ነገሮች የተቀያየሩት ልክ እንደ ሱናሚ በድንገት ነበር። መላው ሆስፒታል በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን ለመርዳት በአዲስ መልክ ተዋቀረ። በዚህ አሳዛኝ ወቅት ታካሚዎቹ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ስለሆኑ ከቤተሰባቸው፣ ከዘመዶቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር በአካል መገናኘት አይችሉም። ስለዚህ ስላሉበት ሁኔታ ለቤተሰቦቻቸው ደውዬ የምናገረው እኔ ነኝ። አንድ ቀን እኩለ ሌሊት ላይ ለአንድ ልጅ ደውዬ አባቱ ሊሞቱ እንደሆነ ማሳወቅ ነበረብኝ። ስለዚህ ስልኬን ተጠቅሜ ልጁን በቪዲዮ ኮንፍረንስ አነጋገርኩት። ይህም አባቱ ራሳቸውን ባያውቁም ከመሞታቸው በፊት ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያያቸው አስችሎታል። በጣም ልብ የሚሰብር ነገር ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትህ ያጽናናህ እንዴት ነው?
ጃንዶሜኒኮ ጉላ፦ ግራ ከተጋቡትና በጭንቀት ከተዋጡት አብዛኞቹ የሥራ ባልደረቦቼ በተለየ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ሚዛኔን ለመጠበቅ ረድቶኛል። ይሖዋ ለዚህ አስቸጋሪ ወቅት አስቀድሞ እንዳዘጋጀን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተረድቻለሁ። ይህ ወረርሽኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ መሆኑን ማወቄ ሁኔታውን በሚዛናዊነት ለመመልከት ረድቶኛል። እምነቴ በእጅጉ ጨምሯል።
ከይሖዋ ያገኘኸው መጽናኛ ሌሎችን ለማጽናናት የረዳህ እንዴት ነው?
ጃንዶሜኒኮ ጉላ፦ የአምላክ መንፈስ በእጅጉ እንደረዳኝ ይሰማኛል። ይህ መንፈስ በቤተሰብ ሕይወቴና በሥራ ቦታዬ እንደሚረዳኝ ሁሉ በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ወንድሞቼን መደገፍ እንድችልም ረድቶኛል።
ይሖዋ ቤተሰብህን ለማጽናናት እንድትችል የረዳህ እንዴት ነው?
ጃንዶሜኒኮ ጉላ፦ ሆስፒታሉ ውስጥ ረዘም ያለ ሰዓት መሥራት ቢጠበቅብኝም ከቤተሰቤ ጋር መንፈሳዊ ነገሮችን ማድረጌን አላቆምኩም። ይህም ባለቤቴን በጣም አበረታቷታል። አንድነታችን ይበልጥ ተጠናክሯል። የቤተሰብ አምልኳችን ሦስት ዓመት ገደማ የሆናትን ልጃችንን ጂኔቭራን ለማጽናናትም ረድቶኛል። ነገሮች እንደተለዋወጡ ስለሚገባት ‘ኮሮና ቫይረስ ስላለ አባዬ ሥራ እንዲሄድ አልፈልግም’ ወይም ‘አባዬ ተመልሶ ባይመጣስ እያልኩ እፈራለሁ’ በማለት ስጋቷን የምትገልጽበት ጊዜ አለ። እሷን ለማረጋጋት ኦሪጅናል መዝሙሮች እንከፍትላታለን፤ ብዙም ሳይቆይ መሳቅ ትጀምራለች።
የሥራ ባልደረቦችህን እንዴት እንዳጽናናሃቸው ልትነግረን ትችላለህ?
ጃንዶሜኒኮ ጉላ፦ አንድ የሥራ ባልደረባዬ በቅርቡ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምሯል። የተዋወቅነው ቀደም ሲል በምሠራበት ሆስፒታል ውስጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት ነበር፤ በወቅቱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተወያይተን ነበር። ማጥናት የጀመረው ወረርሽኙ ከመከሰቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ነበር። በአሁኑ ወቅት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በሳምንት ሁለቴ የምናጠናበት ጊዜ አለ። አንድ ቀን እንዲህ ብሎ ስሜቱን ሲገልጽልኝ ልቤ በጣም ተነካ፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ ሕይወቴን እንዳስተካክል እየረዳኝ ነው። አሁን ውስጣዊ ሰላም አግኝቻለሁ። የሰው ልጆች የተፈጠሩት ለምን እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ፤ እንዲሁም አሁን ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ላሉኝ ጥያቄዎች መልስ እያገኘሁ ነው። እምነቴ እያደገ ስለሆነ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ እንዳልሰጋ ረድቶኛል፤ ተስፋ እንዲኖረኝም አድርጓል።”
በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች ማጽናናት የቻልከው እንዴት ነው?
ጃንዶሜኒኮ ጉላ፦ በጣም የሚያሳዝነው፣ በጉባኤያችን ውስጥ ያለች አንዲት እህት [እህት ዳንኤላ ስግሬቫ] በኮቪድ-19 በመያዟ ሆስፒታል መግባት ነበረባት። አምቡላንስ ካላቸው ሁለት ወንድሞች ጋር ተነጋግሬ እሷን ወደ ሆስፒታል እንዲያመጧት ዝግጅት አደረግን። ወንድሞች እሷን ለማምጣት ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘዋል። እነሱን ስታያቸው ደስታዋ ወሰን አልነበረውም! በዚያ አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ሆና ወደ ሆስፒታሉ ድንገተኛ ክፍል መጥታ እኛን ስታገኘን በእጅጉ ተጽናናች። እኔም ጥሩ አቀባበል አደረግኩላት፤ ሁላችንም የሕክምና ባለሙያዎች ስለሆንን በወንድሞቿ መከበብ ችላለች። ወንድሞች ፍቅር ስላሳዩአትና ስለደገፏት በጣም ተበረታታች። “ይሖዋ ስሜታችንን እንደሚረዳልን ከድሮም ጀምሮ አውቅ ነበር፤ አሁን ግን ያደረገልኝ ነገር ከጠበቅኩት በላይ ነው” በማለት ምስጋናዋን ገልጻለች።
ይሖዋ ለዕለቱ የሚያስፈልገኝን እርዳታ እንደሚሰጠኝ እተማመናለሁ። በየቀኑ ወደ ሥራዬ በመኪና ስሄድና ከሥራ ስመለስ ኦሪጅናል መዝሙሮች አዳምጣለሁ፤ ይህም የሚያስፈልገኝን መንፈሳዊና ስሜታዊ ጥንካሬ ይሰጠኛል። ይሖዋን ላደረገልኝ ነገር ከልብ አመሰግነዋለሁ። ይሖዋ አብሮን ነው ሁሌም የሚለውን መዝሙር ስሰማ ‘ይሖዋ አብሮኝ ነው ሁሌም። እጄን ይዞ፤ መንገድ መራኝ። አይለይም ከኔ’ የሚሉትን ስንኞች አብሬ እዘምራለሁ።