በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መርከቦች በሩዎን፣ ፈረንሳይ በፌስቲቫሉ ለመካፈል ወደብ ላይ ተሰልፈው። አነስ ያሉት ፎቶግራፎች፡- ወንድሞችና እህቶች ዝግጅቱ በሚካሄድበት ቦታ አቅራቢያ የጽሑፍ ጋሪዎችን ተጠቅመው ሲመሠክሩ

ነሐሴ 18, 2023
ፈረንሳይ

በሩዎን፣ ፈረንሳይ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የመርከቦች ፌስቲቫል ላይ የአደባባይ ምሥክርነት ተሰጠ

በሩዎን፣ ፈረንሳይ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የመርከቦች ፌስቲቫል ላይ የአደባባይ ምሥክርነት ተሰጠ

የፈራንሳይዋ ሩዎን ከተማ በየአራት ዓመቱ በሚደረግ ልዩ ዝግጅት ላይ ብዛት ያላቸውን ባለሸራ መርከቦች ታስተናግዳለች፤ ይህ ልዩ ዝግጅት ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ መርከቦች ባሕር ላይ የሚሰባሰቡበት ነው። በዚህ ዓመት ዝግጅቱ የተካሄደው ከሰኔ 8 እስከ 18 ሲሆን ከተለያዩ አገራት የመጡ ስድስት ሚሊዮን ጎብኚዎች ተገኝተዋል። ዝግጅቱ በተካሄደበት በእያንዳንዱ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች በ12 የተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ላይ የጽሑፍ ጋሪዎችን ይዘው በመቆም ምሥክርነት ሰጥተዋል። ቁጥራቸው ከ600 የሚበልጥ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ሥራ የተሳተፉ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማነጋገር ችለዋል።

ቀደም ሲል ፎቶግራፍ በማንሳት ሙያ ተሰማርቶ የነበረ አንድ ሰው ጋሪውን በመጠቀም ወደሚያገለግሉት ወንድሞች ቀርቦ፣ የሚያሳዩትን ደግነት የተሞላበትና ወዳጃዊ አቀራረብ እንዳስተዋለ ገለጸላቸው። ወንድሞችም ግለሰቡ ከሰጠው ሐሳብ በመነሳት በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች ፍቅር የማያሳዩት ለምን እንደሆነ በሰፊው አወያዩት። ከዚያም 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5⁠ን ካነበቡለትና ካብራሩለት በኋላ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር አበረከቱለት። ሰውየው በድጋሚ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መወያየት እንደሚፈልግ የነገራቸው ሲሆን አድራሻውንም ሰጥቷቸዋል።

በሌላ ጊዜ ደግሞ አንዲት ወጣት ሴት ወደ ጋሪው ሄዳ እንዲህ በማለት ጠየቀች፦ “ኢየሱስ ከሞተና ከተነሳ የሞቱ ወዳጆቻችን እስካሁን ድረስ ትንሣኤ ያላገኙት ለምንድን ነው? ወንድ አያቴንና ሴት አያቴን በሞት አጥቻለሁ፤ በድጋሚ ላያቸው እናፍቃለሁ።” በምላሹም እህታችን ለወጣቷ ሴት ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን ማጽናኛ የሚለውን ቪዲዮ አሳየቻት። ከውይይቱ በኋላ ወጣቷ ሴት አንድ ብሮሹር የተበረከተላት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ ተቀብላለች።

በፈረንሳይ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ‘ምሥራቹን ለሌሎች ለማካፈል’ ራሳቸውን በፈቃደኝነት ማቅረባቸው የሚያስደስት ነው።—1 ቆሮንቶስ 9:23