በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኖርሞንዲ፣ ፈረንሳይ ውስጥ የሚገኘው የአሁኑ ቅርንጫፍ ቢሮ

ግንቦት 30, 2023
ፈረንሳይ

ኖርሞንዲ የሚገኘው የፈረንሳይ ቤቴል 50 ዓመት ሞላው

ኖርሞንዲ የሚገኘው የፈረንሳይ ቤቴል 50 ዓመት ሞላው

ጥር 2023 በፈረንሳይ፣ ኖርሞንዲ ክልል የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ሥራ ከጀመረ 50 ዓመት አስቆጠረ። ቅርንጫፍ ቢሮው ለይሖዋ አገልግሎት የተወሰነው፣ ሥራ ከጀመረ ከስድስት ወር ገደማ በኋላ ማለትም ሰኔ 9, 1973 ነው።

የኖርሞንዲው ሕንፃ ከመገንባቱ በፊት ቅርንጫፍ ቢሮው ሙሉ በሙሉ ሥራውን የሚያከናውነው፣ በፓሪስ አቅራቢያ በሚገኘው በቡሎኝ-ቢሎኩር ከተማ ሆኖ ነበር። ይሁንና በአገሪቱ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ከመጣው የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር አንጻር እየሰፋ የመጣውን ሥራ ለማስተናገድ ቢሮው የሚመጥን አልሆነም። በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ ታትሞ ወደ ፈረንሳይ የሚመጣው ጽሑፍ የሚወርደው ለ አቭር በተባለች በስተ ምዕራብ የምትገኝ የወደብ ከተማ ላይ ነበር፤ ይህች ከተማ ደግሞ በወቅቱ ከነበረው ቅርንጫፍ ቢሮ 200 ኪሎ ሜትር ገደማ ትርቃለች። ይህ ከጊዜ እንዲሁም ከመጓጓዣና ከሌሎች ወጪዎች አንጻር የሚፈጥረውን ጫና ለመቀነስ በማሰብ ወንድሞች በሁለቱ ከተሞች አማካይ ቦታ ላይ የሚገኝ መሬት መፈለግ ጀመሩ፤ ዓላማቸውም ተጨማሪ የቤቴል ሕንፃዎች መገንባት ነበር።

በመጨረሻም ወንድሞች በኖርሞንዲ ክልል በምትገኘው ትንሿ የሉቪዬ ከተማ የሚፈልጉት ዓይነት መሬት አገኙና ገዙ፤ ቦታው ከፓሪስም ሆነ ከለ አቭር ከተሞች 100 ኪሎ ሜትር ገደማ አማካይ ቦታ ላይ የሚገኝ ነው። በ1972 ግንባታ ተጀመረ፤ ከስምንት ወራት በኋላም ተጠናቀቀ።

ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት የአገሪቱ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር መጨመሩን ቀጥሏል። ይህን እድገት ለማስተናገድ በኖርሞንዲ ቤቴል ላይ በተደጋጋሚ የማስፋፊያ ሥራ ማካሄድ ግድ ሆኗል። በኋላ ላይ በአቅራቢያው ባለ ቦታ መሬት ተገዛ፤ ለመኖሪያ የሚያገለግሉ ተጨማሪ ሕንፃዎችም ተገነቡበት። በ1996 ደግሞ በቡሎኝ-ቢሎኩር ቤቴል የነበሩት ቀሪዎቹ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ወደ ኖርሞንዲ ተዛወሩ።

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን አመለካከት አለህ? የሚለው ትራክት፣ ዛሬ በፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ ከሚተረጎሙት 24 ቋንቋዎች በ20ዎቹ

በአሁኑ ወቅት የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ በ13 አገራት ውስጥ ከ162,000 በላይ አስፋፊዎች የሚያከናውኑትን የስብከት ሥራ በበላይነት ይከታተላል። በኖርሞንዲ ቤቴል የሚከናወነው የሕትመት ሥራ በ1998 ቢያቆምም ሕንፃዎቹ አስፈላጊው የዲዛይን ለውጥ ተደርጎባቸው የስብከቱንና የማስተማሩን ሥራ ለሚደግፉ ሌሎች የሥራ ዘርፎች እያገለገሉ ነው። ከእነዚህ አንዱ የትርጉም ሥራ ሲሆን በዚህ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በ24 ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ይተረጎማሉ። በተጨማሪም ቅርንጫፍ ቢሮው ከቪዲዮ ቀረፃ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውናል። በአሁኑ ወቅት ከ400 በላይ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ያገለግላሉ።

ይሖዋ በፈረንሳይ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ ‘ሲያፋጥነው’ በማየታችን በጣም ደስተኞች ነን!—ኢሳይያስ 60:22