የካቲት 25, 2022
ፈረንሳይ
የማቴዎስ ወንጌል በፈረንሳይ የምልክት ቋንቋ ወጣ
የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዲዲዬር ኮህለር የማቴዎስ ወንጌል መጽሐፍ ቅዱስ በፈረንሳይ የምልክት ቋንቋ መውጣቱን የካቲት 19, 2022 አብስሯል። መጽሐፉን ከjw.org እና ከJW Library Sign Language አፕሊኬሽን ላይ ማውረድ ይቻላል። ይህ መጽሐፍ የይሖዋ ምሥክሮች በፈረንሳይ የምልክት ቋንቋ ያወጡት የመጀመሪያው የአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ነው።
መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱ የተነገረበትን ፕሮግራም 1,500 ገደማ ሰዎች እንደተመለከቱት ይገመታል። ወንድም ኮህለር በንግግሩ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የፈረንሳይ የምልክት ቋንቋ፣ ስሜት መግለጽ የሚጠይቅ ቋንቋ ነው። ግለሰቡ በፊቱ፣ በዓይኖቹና በመላ ሰውነቱ የገጸ ባሕርያቱን ስሜትና ዝንባሌ ማንጸባረቅ ይጠበቅበታል። በመሆኑም አንድም መረጃ አያመልጠንም! በጽሑፍ የሰፈረው ቃል ይበልጥ ሕያው ይሆናል ማለት ይቻላል!”
የይሖዋ ምሥክሮች ከ1960ዎቹ መጨረሻ አንስቶ በፈረንሳይ የምልክት ቋንቋ የስብከቱን ሥራ ሲያደራጁ ቆይተዋል። በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የመጀመሪያው የፈረንሳይ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ በፓሪስ ዳርቻ በሚገኘው በቪንሰንስ ተቋቋመ። ከዚያም በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ የበላይ አካሉ፣ የፈረንሳይ የምልክት ቋንቋ የርቀት ትርጉም ቢሮ እንዲመሠረት ለፈረንሳይ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ፈቃድ ሰጠ። በ2019 ወረርሽኙ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ የትርጉም ቡድኑ በሉቪዬ፣ ፈረንሳይ ወደሚገኘው ቤቴል ተዛወረ። በዛሬው ጊዜ በፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ሥር 11 የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችና 39 ቡድኖች ይገኛሉ።
የፈረንሳይ የምልክት ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ የጀመረው በማቴዎስ ወንጌል ነው። ቀጥሎ የሚወጣው ደግሞ የዮሐንስ ወንጌል ነው። የኢየሱስን ሕይወት የሚተርኩት እነዚህ ሁለት መጻሕፍት በሚገባ ይታወቃሉ፤ በትረካ መልክ የተጻፉ በመሆናቸው ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ጋር ሲነጻጸሩ ለመተርጎም ቀለል ይላሉ። የማቴዎስ ወንጌል ከመውጣቱ በፊት አስፋፊዎች በፈረንሳይ የምልክት ቋንቋ ማግኘት የሚችሉት የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ብቻ ነበር።
የትርጉም ቡድኑ አባል የሆነች መስማት የተሳናት አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ልጅ ሳለሁ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው በተባለው መጽሐፍ ላይ ያሉትን ሥዕሎች ደጋግሜ አይ ነበር። የማቴዎስን መጽሐፍ በፈረንሳይ የምልክት ቋንቋ ስመለከት እነዚያ ሥዕሎች ትዝ አሉኝ። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ መልእክቱን ሙሉ በሙሉ መረዳት ቻልኩ።”
ሌላ የትርጉም ቡድኑ አባል ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆቼ መስማት የተሳናቸው ስለሆኑ በፈረንሳይ የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲዘጋጅላቸው እመኝ ነበር። በትርጉም ሥራው እካፈላለሁ ብዬ ግን ጨርሶ አስቤ አላውቅም። ግሩም ስጦታ ነው!”
የማቴዎስ ወንጌል በፈረንሳይ የምልክት ቋንቋ በመውጣቱ በጣም ተደስተናል። ይህ መጽሐፍ መውጣቱ ይሖዋ ሁሉም ሰው “የሕይወትን ውኃ በነፃ” እንዲወስድ እየጋበዘ እንደሆነ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።—ራእይ 22:17