ኅዳር 12, 2020
ፊሊፒንስ
በተከታታይ የተከሰተ ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ በፊሊፒንስ ከፍተኛ ጉዳት አስከተለ
ቦታው
ደቡባዊ ሉዞን እና በአቅራቢያው ያሉ ደሴቶች
የደረሰው ጉዳት
ጥቅምት 25, 2020 ፊሊፒንስ ውስጥ በሉዞን ግዛት በባይኮል ክልል በምትገኘው በአልቤይ አውራጃ ሞላቭ (በፊሊፒንስ ኪንታ ተብሎ ይጠራል) የተባለ ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ ተከስቶ ነበር። ይህ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ መላውን የሉዞን ደሴት አዳርሷል
ኅዳር 1, 2020 ደግሞ ጎኒ (በፊሊፒንስ ሮሊ ተብሎ ይጠራል) የተባለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በሉዞን ግዛት በባይኮል ክልል በምትገኘው በካታንዱዋንስ ደሴት ተከስቶ ነበር። አምስተኛ እርከን የተሰጠው ይህ አውሎ ነፋስ ቀደም ሲል ሞላቭ በተባለው አውሎ ነፋስ በተመቱ ሌሎች አውራጃዎችም ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል
በእነዚህ ዝናብ የቀላቀሉ አውሎ ነፋሶች ምክንያት በአካባቢው ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከስቷል፤ የኤሌክትሪክ ኃይልና የመጠጥ ውኃ አቅርቦትም ተቋርጧል። በአደጋው በተጎዱ አካባቢ ካሉት ጋር መገናኘትም በጣም አስቸጋሪ ነው
በወቅቱ የጣለው ዶፍ ዝናብ ከማዮን ተራራ ከባድ የጭቃ ጎርፍ እንዲነሳና በተራራው አቅራቢያ ባሉ ቤቶች ላይ ከባድ ጉዳት እንዲከሰት አድርጓል
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ ያደረሰው ጉዳት
በመቶዎች የሚቆጠሩ አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፤ ወይም አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ተደርገዋል
አንዲት የ89 ዓመት እህት ቤታቸውን ለቅቀው ሲወጡ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ ወድሟል
በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት
134 መኖሪያ ቤቶችና 8 የስብሰባ አዳራሾች መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል
75 መኖሪያ ቤቶችና 8 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
101 መኖሪያ ቤቶችና 1 የስብሰባ አዳራሽ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል
እርዳታ ለመስጠት የተደረገው ጥረት
የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና በአካባቢው ያሉ ሽማግሌዎች ስድስት የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ወንድሞች በቂ ምግብ፣ ውኃ፣ መጠለያና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እንዲያገኙ ለመርዳት ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል። ወንድሞች እርዳታ ሲሰጡና ሌሎችን ሲያጽናኑ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የወጡትን መመሪያዎች ለማክበር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል
በእነዚህ የተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ወንድሞቻችን መጸለያችንን እንቀጥላለን። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት “የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው” ይሖዋ ወንድሞቻችንን እንደሚረዳቸው እርግጠኞች ነን።—2 ቆሮንቶስ 1:3