በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት የተነሳ ፎቶግራፍ፤ ማየትና መስማት የተሳናት የሆነችውና በዕድሜ የገፋችው እህት ሲንቲያ (በስተ ግራ) በጉባኤዋ ውስጥ ካለች እህት ጋር በታክታይል ምልክት ቋንቋ አማካኝነት ስትነጋገር

ግንቦት 12, 2020
ፊሊፒንስ

በወረርሽኙ ወቅት አንድ ጉባኤ ማየትና መስማት ለተሳናት እህት ያደረገው ድጋፍ

በወረርሽኙ ወቅት አንድ ጉባኤ ማየትና መስማት ለተሳናት እህት ያደረገው ድጋፍ

ፊሊፒንስ ውስጥ የምትኖረው እህት ሲንቲያ ፓብሎ በፓንግሁሎ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ የምታገለግል የ64 ዓመት ያልተጠመቀች አስፋፊ ነች። እህት ሲንቲያ ማየትና መስማት የተሳናት ከመሆኗም ሌላ ገቢዋ በጣም ዝቅተኛ ነው። የምትኖረው ብዙ ሕዝብ በሚበዛበት የቫሌንዙዌላ ከተማ ውስጥ ከሚኖሩ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ዘመዶቿ ጋር ነው። ሲንቲያ ያለችበት ሁኔታ በራሱ ተፈታታኝ ቢሆንም ይህ ወረርሽኝ ደግሞ ችግሯን አባብሶታል፤ በጉባኤዋ ውስጥ ያሉ ወንድሞች ግን እሷን ለመንከባከብ ጥረት እያደረጉ ነው።

ወንድም ዎልተር ኢሉሚን የታጠቡ ልብሶችንና የእርዳታ ቁሳቁሶችን በሞተር ብስክሌቱ ለሲንቲያ ሲወስድላት

ሲንቲያ ዕድሜዋ የገፋ በመሆኑ ለኮቪድ-19 ተጋላጭ ከሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች መካከል ትመደባለች። ወረርሽኙ እሷ በምትኖርበት አካባቢ የውኃ እጥረት እንዲከሰት ስላደረገ ልብሷን ለማጠብ ተቸግራለች። ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት የጉባኤዋ እህቶች ልብሷን ያጥቡላት ነበር፤ አሁን ግን መንግሥት በጣለው እገዳ ምክንያት ይህን ማድረግ አልቻሉም።

የሲንቲያ ጉባኤ ሽማግሌ የሆነ ዎልተር ኢሉሚን የተባለ ወንድም ከቤቱ ወጥቶ ሲንቲያን ለመንከባከብ የሚያስችል ልዩ ፈቃድ ከባለሥልጣናቱ አገኘ። ይህ ፈቃድ የሚሰጠው ወሳኝ አገልግሎት ለሚያከናውኑ ሰዎች ብቻ ነው። ዎልተር የሲንቲያን ልብስ ከማጠብ በተጨማሪ ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችንም ይወስድላታል። ይህን ሲያደርግ ማስክና ሌሎች መከላከያዎችን ማድረግን እንዲሁም እጁን አዘውትሮ መታጠብን ጨምሮ መንግሥት ያወጣቸውን መመሪያዎች በሙሉ ይከተላል።

እህት ሲንቲያ ለወንድሞችና ለእህቶች ያላትን አመስጋኝነት የሚገልጹ አጫጭር የቪዲዮ መልእክቶችን ትቀረጻለች። ከዚያም ወንድም ዎልተር ቪዲዮዎቹን ለጉባኤው ያሳያል።

ሲንቲያ ከወረርሽኙ በፊት በስብከቱ ሥራ ስትካፈል

በተጨማሪም ወንድም ዎልተር ወደ ሲንቲያ ቤት እየሄደ ጉባኤው በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የሚያደርገውን ስብሰባ በታክታይል ምልክት ቋንቋ ያስተረጉምላታል። በመሆኑም ሲንቲያ በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ አዘውትራ ሐሳብ መስጠት ችላለች። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በስብሰባ ላይ ተሳትፎ ማድረጓ ስብሰባውን የሚከታተሉ ሌሎች ሰዎችንም ያበረታታል።

ይሖዋ ሕዝቦቹ ‘ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ሲያዩ ከበፊቱ ይበልጥ’ አንዳቸው ለሌላው ማጽናኛና እርዳታ እየሰጡ መሆኑን ሲያይ እንደሚደሰት ጥርጥር የለውም።—ዕብራውያን 10:24, 25