በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ የጊልያድ ምሩቅ የሆነው ወንድም ቪክቶር ኋይት በሚንዳናው፣ ፊሊፒንስ ንግግር ሲያቀርብ። በስተ ቀኝ፦ በፊሊፒንስ ካገለገሉት የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን አንዳንዶቹ

ሰኔ 14, 2022
ፊሊፒንስ

በፊሊፒንስ የሚስዮናውያን ሥራ 75 ዓመት አስቆጠረ

በፊሊፒንስ የሚስዮናውያን ሥራ 75 ዓመት አስቆጠረ

ሰኔ 14, 1947 ሎሬንዞ አልፒቼ፣ ኧርል ስቱዋርት እና ቪክቶር ኋይት የተባሉትን ሦስት ወንድሞች የያዘው መርከብ ማኒላ ደረሰ። በፊሊፒንስ የተመደቡት የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን እነሱ ነበሩ። በጊልያድ የሠለጠነ ኒክ ስኬልፓሪክ የተባለ ሌላ ሚስዮናዊ ደግሞ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ተቀላቀላቸው።

እነዚህ ወንድሞች በሚገባ የሠለጠኑ ከመሆኑም ሌላ ለሥራ ዝግጁ ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ፣ በፊሊፒንስ በስብከቱ ሥራ እየተካፈሉ የነበሩትን 2,400 አስፋፊዎች በመርዳቱ ሥራ ተጠመዱ። ከ11 ዓመት በኋላ ማለትም በ1958 አማካይ የአስፋፊዎች ቁጥር በአሥር እጥፍ ገደማ አድጎ ከ23,000 በላይ ሆነ። አሁን ደግሞ፣ ማለትም የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን ፊሊፒንስ ከገቡ ከ75 ዓመት በኋላ በአገሪቱ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች ቁጥር ከ230,000 በላይ ደርሷል።

ወንድም ሚልተን ሄንሸልና ወንድም ናታን ኖር በማኒላ ስብሰባው በተካሄደበት ቦታ

የሚስዮናውያኑ መምጣት የአጋጣሚ ጉዳይ አልነበረም። እነሱ ከመምጣታቸው ከሦስት ወር ገደማ በፊት፣ በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ወንድም ናታን ኖር ከመጋቢት 31 እስከ ሚያዝያ 2, 1947 በማኒላ በተካሄደ ታሪካዊ ስብሰባ ላይ ንግግር አቅርቦ ነበር። ወንድም ኖር፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለውን ውድመት ተከትሎ የስብከቱን ሥራ ለማደራጀት በጊልያድ የሠለጠኑ ሚስዮናውያን በቅርቡ ወደ አገሪቱ እንደሚላኩ ለተሰብሳቢዎቹ ቃል ገብቶላቸው ነበር።

በስተ ግራ፦ “ውዳሴ የሚያቀርቡ ሕዝቦች” በተባለው ትልቅ ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን ማለትም መጋቢት 31, 1947 በስብሰባው ላይ የተገኙት አድማጮች። በስተ ቀኝ፦ ወንድም ሚልተን ሄንሸል ንግግር ሲያቀርብ

በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ላይ 151 አዳዲስ ወንድሞችና እህቶች በጦርነቱ ወቅት የሰመጡ መርከቦች ባሉበት የማኒላ የባሕር ወሽመጥ ተጠመቁ። በዚያው ዕለት ወንድም ኖር 4,200 ገደማ አድማጮች በተገኙበት “የሕዝቦች ሁሉ ደስታ” በሚል ርዕስ የሕዝብ ንግግር አቀረበ። ንግግሩ በመላዋ አገሪቱ ለሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ አድማጮች በሬዲዮ የቀጥታ ስርጭት ተላልፎ ነበር። ወንድም ኖርና ከዋናው መሥሪያ ቤት አብሮት የመጣው ወንድም ሚልተን ሄንሸል፣ ወንድሞች በተደራጀ መንገድ የስብከቱን ሥራ ማከናወናቸውን እንዲቀጥሉ ለመርዳት ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻ ሰጧቸው።

በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ማለትም ሚያዝያ 2, 1947 በማኒላ የባሕር ወሽመጥ ከተጠመቁት 151 ወንድሞችና እህቶች መካከል አንዳንዶቹ

ከ1954 አንስቶ ፊሊፒንስ ውስጥ በሚስዮናዊነት ያገለገለው ወንድም ዴንተን ሆፕኪንሰን ባለፉት 75 ዓመታት የተካሄደውን ሥራ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “በ1947 የመጡት የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን ጉባኤዎቹን ለማነጽና ለማደራጀት እንዲሁም ከዚያ በኋላ ለመጣው ከፍተኛ እድገት ለማዘጋጀት ብዙ ሥራ አከናውነዋል።”

የሰማዩ አባታችን ይሖዋ በፊሊፒንስም ሆነ በመላው ዓለም ያሉት አገልጋዮቹ በትጋት ያከናወኑትን ሥራ በመባረኩ እናመሰግነዋለን።—ኢሳይያስ 60:22