በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ባለፉት ዓመታት ውስጥ በታጋሎግ ቋንቋ የወጡ መጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች

ነሐሴ 30, 2022
ፊሊፒንስ

የታጋሎግ አንባቢዎች መጠበቂያ ግንብ መጽሔትን በቋንቋቸው ማንበብ ከጀመሩ 75 ዓመታት ተቆጠሩ

የታጋሎግ አንባቢዎች መጠበቂያ ግንብ መጽሔትን በቋንቋቸው ማንበብ ከጀመሩ 75 ዓመታት ተቆጠሩ

መጠበቂያ ግንብ በታጋሎግ ቋንቋ መተርጎም ከጀመረ 75 ዓመት የሞላው ዘንድሮ መስከረም 1, 2022 ነው። መጽሔቱ መተርጎም በጀመረበት ጊዜ አንዱ እትም 600 ገደማ በሚሆኑ ቅጂዎች ይሰራጭ ነበር፤ አሁን ግን እያንዳንዱ እትም ከ1.2 ሚሊዮን በሚበልጡ የታተሙ ቅጂዎች ይሰራጫል። በተጨማሪም jw.org ላይ የመጽሔቱን የኤሌክትሮኒክ ቅጂ ማግኘት ይቻላል።

ምሥራቹ ወደ ፊሊፒንስ የደረሰው በ1908 ነው። በ1924 ቅርንጫፍ ቢሮው ከተቋቋመ በኋላ የስብከቱን ሥራ ይበልጥ በተደራጀ መንገድ ማከናወን ተቻለ። በወቅቱ በስብከቱ ሥራ ላይ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉት እንግሊዝኛ ጽሑፎች ነበሩ፤ ወንድሞች ግን ጽሑፎቹን ወደ ታጋሎግ የመተርጎሙን አስፈላጊነት ተገንዝበው ነበር።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ማለትም ሰኔ 14, 1947 ኧርል ስቱዋርት፣ ቪክቶር ዋይትና ሎረንዞ አልፒቼ የተባሉ ጊልያድ ገብተው የሠለጠኑ ሚስዮናውያን ወደ ፊሊፒንስ መጡ። በወቅቱ የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ ሆኖ የተሾመው ወንድም ስቱዋርት ብቃት ያላቸው ወንድሞች መጠበቂያ ግንብን ወደ ታጋሎግ እንዲተረጉሙ ወዲያውኑ ዝግጅት አደረገ። በዚያኑ ዓመት መስከረም ወር ላይ አስፋፊዎች በወር ሁለቴ የሚወጣውን የመጠበቂያ ግንብ እትም ማሰራጨት ቻሉ።

ሂላሪዮን አሞሬስ የታጋሎግ ትርጉም ሥራ ሲጀመር ከነበሩት ተርጓሚዎች መካከል አንዱ ነው

ያኔ ከነበሩት ተርጓሚዎች መካከል አብዛኞቹ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር ሲሉ ቀን ላይ ሰብዓዊ ሥራ ይሠራሉ፤ ከዚያም ምሽት ላይ ጽሑፎቹን ይተረጉማሉ። ከተርጓሚዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ወንድም ሂላሪዮን አሞሬስ እንዲህ ብሏል፦ “እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት ድረስ የምንሠራበት ጊዜ ነበር። ግን ወንድሞች የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ አስተዋጽኦ ስላደረግን ደስተኞች ነበርን።”

በአሁኑ ጊዜ በፊሊፒንስ በታጋሎግ ቋንቋ በሚካሄዱ 1,126 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 97,443 አስፋፊዎች አሉ። በአገሪቱ ውስጥ 76.5 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የታጋሎግ ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሉ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ደግሞ ከ115,000 የሚበልጡ የታጋሎግ ቋንቋ ተናጋሪ አስፋፊዎች አሉ። በታጋሎግ ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎች በሌሎች በርካታ አገሮች ውስጥ ይሰራጫሉ፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ የታጋሎግ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ አስፋፊዎችና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች እነዚህን ጽሑፎች ያነብባሉ።

ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት በዓለም ዙሪያ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ በማድረጉ ምንኛ አመስጋኞች ነን።—ማቴዎስ 24:45, 46