በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በአደጋው ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው 195 የወንድሞቻችን ቤቶች መካከል አንዱ

ኅዳር 18, 2019
ፊሊፒንስ

የፊሊፒንስ ደቡባዊ ክፍል በተደጋጋሚ በምድር መናወጥ ተመታ

የፊሊፒንስ ደቡባዊ ክፍል በተደጋጋሚ በምድር መናወጥ ተመታ

ደቡባዊ ፊሊፒንስ ከጥቅምት 16, 2019 አንስቶ በተከታታይ በተከሰቱ ኃይለኛ የምድር መናወጦች ተመትታለች፤ በዚህም ሳቢያ 21 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ከ400 የሚበልጡ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከ35,000 የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ የምድር መናወጦች መካከል ቢያንስ ሦስቱ በመሬት መንቀጥቀጥ መለኪያ ከ6.0 በላይ ያስመዘገቡ ናቸው። በአካባቢው ቀላል የምድር ነውጦች መከሰታቸውን ቀጥለዋል። አንዲት እህት ቀላል ጉዳት ቢደርስባትም በአደጋው ሕይወቱን ያጣ የይሖዋ ምሥክር የለም።

አራት የስብሰባ አዳራሾችና 195 የወንድሞች ቤቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ 9 የስብሰባ አዳራሾችና 351 መኖሪያ ቤቶች መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በርካታ ወንድሞቻችን የሚገኙት በድንኳን ውስጥ ነው፤ ምክንያቱም በቤታቸው ውስጥ መኖር ለደህንነታቸው አስጊ ነው።

የፊሊፒንስ ቅርንጫፍ ቢሮ የተጎዱ ወንድሞችን ለመርዳት ሁለት የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል። ስድስት የቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች የሚያስፈልገውን መንፈሳዊ ማበረታቻ ለመስጠት በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ጎብኝተዋል፤ ከእነዚህ ተወካዮች መካከል ሦስቱ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት ናቸው።

ይሖዋ በዚህ የምድር ነውጥ ጉዳት የደረሰባቸውን ወንድሞቻችን መርዳቱን እንዲቀጥል እንጸልያለን።—መዝሙር 70:5