በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በፊሊፒንስ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግሉት ወንድም ኤልናታን ሊ (ከላይ) እና ወንድም እስራኤል አቬዝ (ከታች) በኢንተርኔት አማካኝነት በተደረገው የ2021 ዓለም አቀፍ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ኮንፈረንስ እና ፌስቲቫል ላይ ንግግር ሲሰጡ

ሚያዝያ 26, 2021
ፊሊፒንስ

የ2021 ዓለም አቀፍ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ኮንፈረንስ እና ፌስቲቫል በፊሊፒንስ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን የትርጉም ሥራ ለእይታ አቀረበ

የ2021 ዓለም አቀፍ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ኮንፈረንስ እና ፌስቲቫል በፊሊፒንስ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን የትርጉም ሥራ ለእይታ አቀረበ

ዓለም አቀፉ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ኮንፈረንስ እና ፌስቲቫል ከ12 አገሮች የተውጣጡ የትምህርት ባለሙያዎችን፣ ዓለም አቀፍ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ተመራማሪዎችንና ምሁራንን የሚያሳትፍ ዝግጅት ነው። ይህ ዝግጅት ከየካቲት 21 እስከ መጋቢት 20, 2021 ድረስ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተካሂዷል። በፊሊፒንስ ዲሊማን ዩኒቨርሲቲ ሥነ ቋንቋ ክፍል ውስጥ የሚሠሩትና የዝግጅቱ ሊቀ መንበር የሆኑት ዶክተር ሪካርዶ ኖላስኮ በፊሊፒንስ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግሉ ተወካዮችን በፕሮግራሙ ላይ እንዲገኙ ጋብዘው ነበር። መጋቢት 9, 2021 በትርጉም ሥራ ላይ የሚካፈሉት ወንድም ኤልናታን ሊ እና ወንድም እስራኤል አቬዝ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያከናውኑት የትርጉም ሥራ መግለጫ ሰጥተዋል። ዝግጅቱን 320 ሰዎች በኢንተርኔት አማካኝነት ተከታትለዋል።

ዶክተር ሪካርዶ ኖላስኮ እንደተናገሩት በፊሊፒንስ በተደረገ አገር አቀፍ ጥናት መሠረት ከትምህርት ቤት መጻሕፍት ውጭ በስፋት የሚነበበው መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ከዚህ አንጻር የኮንፈረንሱ አንድ ክፍል “የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ በፊሊፒንስ ቋንቋዎች” የሚል ጭብጥ ያለው መሆኑ ተገቢ ነው። ወንድሞቻችን የሰጡት መግለጫ ጭብጥም ይኸው ነበር።

ወንድም አቬዝ ያቀረበው ንግግር “ትክክለኛ፣ ለመረዳት ቀላል የሆነ ወይስ ሁለቱም? መጽሐፍ ቅዱስን በአገሪቱ ብቻ ወደሚነገሩ ቋንቋዎች መተርጎም ያለው ተፈታታኝ ሁኔታ” የሚል ርዕስ ነበረው። የአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ትክክለኛ ሆኖም ለመረዳት ቀላል የሆነ ትርጉም ለማዘጋጀት ያደረጉትን ጥረት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ወንድም አቬዝ ለአድማጮቹ እንዲህ ሲል ማብራሪያ ሰጥቷል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ዋነኛ ዓላማ መጽሐፍ ቅዱስን ማስተማር ስለሆነ አዲስ ዓለም ትርጉም ጥቂት ተናጋሪዎች ባሏቸው ቋንቋዎች ጭምር እንዲተረጎም ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኢንተርኔት ላይ ወይም ወደ ይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሾች በመሄድ በነፃ ማግኘት ይቻላል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱሱን ራሳችሁ በማንበብ ተርጓሚዎቹ የአምላክን ቃል ትክክለኛ ሆኖም በቀላሉ በሚገባ መንገድ ለማዘጋጀት ባደረጉት ጥረት ምን ያህል እንደተሳካላቸው ማየት ትችላላችሁ።”

ወንድም ሊ “ከሁሉም ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሰዎችን መሰብሰብ፦ ድንበር የማይገድበው የይሖዋ ምሥክሮች የትርጉም ሥራ” በሚል ርዕስ ባቀረበው ንግግር ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት የትርጉም ሥራ ምን ያህል ስፋት እንዳለው መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫው ላይ ከ6,000 የሚበልጡ ተርጓሚዎችና ሌሎች ፈቃደኛ ሠራተኞች በትርጉም ሥራው እንደሚካፈሉ ተናግሯል። በተጨማሪም ሥራው ከተጀመረባቸው ከ1800ዎቹ አንስቶ ከፍተኛ እድገት እስከተመዘገበባቸው እስካለፉት ዓመታት ድረስ ያለውን ታሪክ ገልጿል። በዓለም ላይ በስፋት በመተርጎም ረገድ የመጀመሪያውን ቦታ የያዘው jw.org ኅዳር 2019 ወደ 1,000 ቋንቋዎች በመተርጎም አዲስ ታሪክ እንዳስመዘገበ ጠቅሷል።

ወንድም ሊ ንግግሩን ሲደመድም እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች የሚተረጉሙት ተርጓሚዎች በዓለም ዙሪያ ላሉ አንባቢዎች ትምህርት የሚሰጥና የሚያበረታታ እንዲሁም በቀላሉ የሚገባ ትርጉም የማዘጋጀት ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።”

ስለ ትርጉም ሥራችን ለሌሎች የምናሳውቅበት እንዲህ ያለ አጋጣሚ በማግኘታችን ደስተኞች ነን። አሁን ምሥራቹ ‘በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድና ቋንቋ ሁሉ’ እየተሰበከ እንዳለ ከምንጊዜውም ይበልጥ በግልጽ እየታየ ነው።—ራእይ 14:6