ሚያዝያ 17, 2020
ፊጂ
ሃሮልድ የተባለው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ የቫንዋቱን እና የፊጂን ደሴቶች መታ
ሃሮልድ የተባለው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ ሚያዝያ 5, 2020 በቫንዋቱ ሰሜናዊ ደሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ። ቀጥሎም ወደ ደቡብ ምሥራቅ በመጓዝ ሚያዝያ 8 በፊጂ ደሴቶች ደቡብ ምዕራባዊ ክፍል ላይ ተመሳሳይ ጉዳት አድርሷል። እስካሁን ያገኘናቸው ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከወንድሞቻችን መካከል የአካል ጉዳት የደረሰበትም ሆነ ሕይወቱ ያለፈ የለም።
ከቫንዋቱ ደሴቶች ትልቁ በሆነውና በሰሜናዊ ጫፍ ላይ በሚገኘው በኤስፒሪቱ ሳንቶ 280 ገደማ አስፋፊዎች ይኖራሉ። በዚህ ደሴትና በአጎራባች ደሴቶች ላይ በሕንፃዎችና በሰብል ላይ ከባድ ውድመት ደርሷል። በፊጂ የሚኖሩ 260 ገደማ አስፋፊዎች ከባድ የንብረት ውድመት ደርሶባቸዋል። ውኃ፣ ኤሌክትሪክና ምግብ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል።
የፊጂ ቅርንጫፍ ቢሮ መሠረታዊ የእርዳታ ቁሳቁስ የማከፋፈሉን ሥራ እያደራጀ ነው። የጉባኤ ሽማግሌዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ወንድሞችና እህቶች እረኝነት እያደረጉ ነው። በዚህ አውሎ ነፋስ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ወንድሞቻችን በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ እንዳገኙ ማወቃችን ያስደስተናል።—ምሳሌ 10:22