የካቲት 1, 2021
ፍሬንች ፖሊኔዢያ
አዲስ ዓለም ትርጉም በታሂቲኛ ወጣ
ጥር 30, 2021 አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በታሂቲኛ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት ወጣ። ፕሮግራሙ አስቀድሞ የተቀዳ ሲሆን በፍሬንች ፖሊኔዥያ ለሚገኙ ጉባኤዎች በሙሉ ተላልፏል። መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን ያበሰረው የታሂቲ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሉክ ጋንዤ ነው።
ታሂቲኛ የብዙዎቹ የፍሬንች ፖሊኔዥያ ነዋሪዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው። በዚያ የሚያገለግሉት 1,100 አስፋፊዎች ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጥቅም ያገኛሉ።
ሁለት የትርጉም ቡድኖች ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ተርጉመው ለመጨረስ ስምንት ዓመት ወስዶባቸዋል። አንደኛው ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “በክልላችን ውስጥ በስፋት የሚሠራበት መጽሐፍ ቅዱስ በ19ኛው መቶ ዘመን የተተረጎመ ነው። ቃላቱን መረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። አዲስ ዓለም ትርጉም ግን ትናንሽ ልጆችን ጨምሮ ቋንቋውን ለሚናገር ሰው ሁሉ በቀላሉ ይገባል። ግልጽ፣ ትክክለኛና ተፈጥሯዊ ለዛውን የጠበቀ ትርጉም ነው።”
ይሖዋ፣ ቃሉ እስከ ምድር ዳር እንዲታወቅ በማድረጉ እናመሰግነዋለን። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የቅኖችን ልብ ሲነካ ለማየት ጓጉተናል።—መዝሙር 46:1