በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ነሐሴ 20, 2019
ፓራጓይ

የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ዓለም ትርጉምን በግዋራኒ ቋንቋ አወጡ

የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ዓለም ትርጉምን በግዋራኒ ቋንቋ አወጡ

ነሐሴ 16, 2019 በካፒያታ፣ ፓራጓይ ከሚገኘው የቤቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ በተላለፈው የክልል ስብሰባ ንግግር ላይ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በግዋራኒ ቋንቋ መውጣቱ ተገለጸ። የፓራጓይ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዳንኤል ጎንዛሌዝ በክልል ስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ላይ መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን አብስሯል። በሌሎች 13 ቦታዎች የሚገኙ ተሰብሳቢዎችም ፕሮግራሙን በቪዲዮ ስርጭት የተከታተሉ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሱ ሲወጣ የነበሩት አጠቃላይ ተሰብሳቢዎች ቁጥር 5,631 ነበር።

ፓራጓይ ውስጥ ስፓንኛ ቋንቋ በስፋት የሚነገር ቢሆንም 90 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ነዋሪ አገር በቀል ቋንቋ የሆነውን ግዋራኒ ቋንቋንም ይናገራል። በላቲን አሜሪካ ከሚገኙ አገሮች መካከል አብዛኛው ነዋሪ ተመሳሳይ የሆነ አገር በቀል ቋንቋ የሚናገረው በፓራጓይ ብቻ ነው።

በትርጉም ሥራው ከተካፈሉት ሰዎች መካከል አንዱ እንደገለጸው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከመውጣቱ በፊትም በርካታ ወንድሞችና እህቶች ወደ ይሖዋ የሚጸልዩት የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በሆነው በግዋራኒ ነበር። ይህ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ግን ይሖዋም በግዋራኒ ቋንቋ ያነጋግረናል። ይሖዋ እንደሚወደንና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተን ይሰማናል። አሁን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይሖዋ አባቴ እንደሆነ ይሰማኛል።”

መጽሐፍ ቅዱስ በግዋራኒ ቋንቋ መውጣቱ በፓራጓይ የሚኖሩትን ግዋራኒ ተናጋሪ የሆኑ 4,934 አስፋፊዎች እንደሚጠቅማቸውና ለይሖዋና ለድርጅቱ ያላቸውን አድናቆት እንደሚያሳድግላቸው ጥያቄ የለውም። ይህ ትርጉም፣ አንባቢዎች ውድ ከሆኑት የአምላካችን ሐሳቦች ጥቅም እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።—መዝሙር 139:17