ታኅሣሥ 1, 2020
ፓፑዋ ኒው ጊኒ
አዲስ ዓለም ትርጉም በሂሪ ሞቱ ቋንቋ ወጣ
የፓፑዋ ኒው ጊኒ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኬጋዋሌ ቢያማ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሂሪ ሞቱ ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ። ፕሮግራሙ በፖርት ሞርዝቢ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ አስቀድሞ የተቀዳ ሲሆን ኅዳር 28, 2020 ለተመልካቾች ተላልፏል። ከ7,000 የሚበልጡ ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።
በዓለማችን ላይ ካሉ አገሮች ውስጥ በቋንቋ ብዛት የመጀመሪያዋ በሆነችው በፓፑዋ ኒው ጊኒ 840 ገደማ የሚሆኑ ቋንቋዎች ይነገራሉ። ሂሪ ሞቱ፣ ከአገሪቱ ሦስት የሥራ ቋንቋዎች አንዱ ነው። ወደ 140,000 የሚጠጉ ሰዎች ይህን ቋንቋ ይናገራሉ።
የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኩኩና ጃክ እንዲህ ብሏል፦ “የሂሪ ሞቱ ቋንቋ ተናጋሪዎች የዚህን መጽሐፍ ቅዱስ መውጣት ለረጅም ጊዜ ሲጠባበቁ ቆይተዋል። አዲስ ዓለም ትርጉምን እንደሚወዱት እርግጠኞች ነን፤ ምክንያቱም ግልጽና ለመረዳት ቀላል ነው።”
ስድስት ተርጓሚዎችን ያቀፈ ቡድን ለአሥር ዓመት ያህል በዚህ ፕሮጀክት ተካፍሏል። አንዲት ተርጓሚ እንዲህ ብላለች፦ “አንባቢዎች ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ የአምላክን ስም ማግኘት በመቻላቸው እንደሚደሰቱ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን ስጦታ ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግናለን!”
ይህን አዲስ ትርጉም ለማዘጋጀት የተከናወነውን ሥራ ሁሉ ስናስብ ልክ እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንደሚከተለው ለማለት እንገፋፋለን፦ “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ሰላም ትሰጠናለህ፤ ምክንያቱም የሠራነውን ነገር ሁሉ ያከናወንክልን አንተ ነህ።”—ኢሳይያስ 26:12