በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 17, 2019
ፔሩ

በፑኖ፣ ፔሩ የአይማራ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ለማግኘት የተደረገ ልዩ ዘመቻ

በፑኖ፣ ፔሩ የአይማራ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ለማግኘት የተደረገ ልዩ ዘመቻ

የፔሩ ቅርንጫፍ ቢሮ አገር በቀል ቋንቋ የሆነውን አይማራን ወደሚናገሩ ሰዎች ምሥራቹን ለማድረስ ከግንቦት 1 እስከ ነሐሴ 31, 2019 ልዩ ዘመቻ አካሂዶ ነበር። ዘመቻው በጣም ስኬታማ ነበር። የዘመቻው ተሳታፊዎች 7,893 ጽሑፎችን ያበረከቱ ሲሆን ለ2,500 ጊዜ ያህል ቪዲዮዎቻችንን አሳይተዋል። ዘመቻው ሲደመደም ወንድሞቻችን 381 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አስጀምረው ነበር።

በፔሩ ውስጥ 450,000 ገደማ የሚሆኑ የአይማራ ቋንቋ ተናጋሪዎች አሉ፤ ከእነሱ መካከል 300,000 ገደማ የሚሆኑት የሚኖሩት ፑኖ በተባለው ክልል ውስጥ ነው። በአሁኑ ወቅት አይማራ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ 331 አስፋፊዎች አሉ፤ እነሱም በሰባት ጉባኤዎችና በስምንት ቡድኖች ውስጥ ይሰበሰባሉ። ከክልሉ ስፋት አንጻር በፔሩ ያሉ አስፋፊዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ከቺሊ የመጡ አይማራ ተናጋሪ አስፋፊዎችም በዘመቻው ላይ ተካፍለዋል። ወንድሞቻችን አይማራ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ለማግኘት ሲሉ ከባሕር ወለል በላይ 5,000 ሜትር ከፍታ ድረስ በመውጣት ቅዝቃዜው ዜሮ ዲግሪ ሴልሽየስ በሚደርስባቸው አካባቢዎች ሰብከው ነበር።

አንዱ ቡድን ለበርካታ ሰዓታት ተጉዞ ወደ አንድ አካባቢ ሲደርስ በአቅራቢያው ከሚገኝ መንደር የመጡ ሰዎች ለቀብር ሥነ ሥርዓት ተሰብስበው ነበር። ከዚያም ወንድሞችና እህቶች መጽሐፍ ቅዱስ ሙታንን አስመልክቶ የሚሰጠውን ተስፋ ነገሯቸው። ወንድሞችና እህቶች የመጽሐፍ ቅዱስን አጽናኝ መልእክት ለማድረስ ስለከፈሉት መሥዋዕት የአካባቢው ባለሥልጣናትና የሟች ቤተሰቦች አመስግነዋቸዋል።

በሌላ አካባቢ ደግሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ በሳምንት ሁለቴ እየተሰበሰቡ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ ሰዎችን አገኙ። እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑት በቦሊቪያ ከሚኖር ዘመዳቸው የወሰዷቸውን እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው እና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባሉትን መጻሕፍት ተጠቅመው እንደሆነ አስፋፊዎቹ አስተዋሉ። ሰዎቹ መጻሕፍቱን ያሳተመው ድርጅታችን መሆኑን ሲገነዘቡ ብዙዎቹ ከወንድሞች ጋር ማጥናትና ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ጀመሩ።

በአንደኛው ቡድን ውስጥ አመራር ይሰጥ የነበረው ወንድም አልበርት ኮንዶር የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ በዚህ ዘመቻ ላይ መካፈል በመቻላችን በጣም ተደስተናል። በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ተጠናክሯል፤ ምክንያቱም ጉዞው አስቸጋሪ ስለሆነ ወደ መንደሩ ጉዞ ስንጀምር እንዴት እንደምንደርስ አናውቅም ነበር። እዚያ ከደረስን በኋላ ደግሞ ይሖዋ ማረፊያ ለማግኘት እንዲረዳን ጸለይን። እሱም ረዳን። መጸለዬ እንዲሁም ሌሎች ወንድሞች በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት መመልከቴ አበረታቶኛል።”

ወንድሞችና እህቶች በፑኖ፣ ፔሩ ለሚኖሩ የአይማራ ቋንቋ ተናጋሪዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን የሕይወት ውኃ ማካፈል በመቻላቸው ደስተኞች ናቸው።—ራእይ 22:17