ነሐሴ 19, 2019
ፔሩ
በፔሩ ከተዘጋጁት ስፖርታዊ ውድድሮች ጋር ተያይዞ የይሖዋ ምሥክሮች መጠነ ሰፊ የአደባባይ ምሥክርነት እያካሄዱ ነው
በሊማ፣ ፔሩ እየተካሄደ ካለው ፓን አሜሪካን ጌምስ እና ፓራፓን አሜሪካን ጌምስ ጋር ተያይዞ ወደ 3,000 የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች በልዩ የአደባባይ ምሥክርነት እየተካፈሉ ነው። ሐምሌ 26, 2019 በጀመሩትና እስከ መስከረም 1 ድረስ በሚቆዩት ውድድሮች ላይ ከ8,500 የሚበልጡ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን 250,000 ገደማ የሚሆኑ ቱሪስቶች እንደሚመጡ ይገመታል።
አስፋፊዎች ለጎብኚዎቹ ለመስበክ ሲሉ በ53 ቦታዎች ላይ 100 የጽሑፍ ጋሪዎችን አዘጋጅተዋል። በስፓንኛ፣ በኬችዋ (አያኩቾ)፣ በአይማራ፣ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛና በፖርቱጋልኛ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች በጋሪዎቹ ላይ ተቀምጠዋል። በተጨማሪም መስማት ለተሳናቸውና የመስማት ችግር ላለባቸው ሰዎች ሲባል በፔሩ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ቪዲዮዎችም ቀርበዋል።
የስብከት ዘመቻውን በማደራጀቱ ሥራ የሚካፈለው ወንድም ኬምፕስ ሞራን ሁርታዶ እንዲህ ብሏል፦ “ጎብኚዎቹ ከመላው ዓለም የመጡ በመሆናቸው ይህ ዘመቻ የተለያየ ባሕል ያላቸውን ብዙ ሰዎች ለማነጋገር ይረዳናል። የአደባባይ ምሥክርነት መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማሩ ሥራችን አስፈላጊ ክፍል ነው፤ ይህ ዘዴ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሲሰብኩ በግልጽ ማየት እንዲችሉ ያደርጋል።”
ወንድሞቻችን ስለሚያከናውኑት መጠነ ሰፊ የስብከት እንቅስቃሴ መስማታችን ያስደስተናል። በፔሩ የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ለመስበክ የሚያደርጉትን ጥረት ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚባርከው እንተማመናለን።—የሐዋርያት ሥራ 17:17