በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በፔሩ እንዲያገለግሉ የተመደቡት የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን። ከኋላ (ከግራ ወደ ቀኝ)፦ ኤቭሊን ቤሪ፣ ቬርዳ ፑል፣ ዎልተር አኪን፣ ኔሊና ፑል እና ሄዘል ትሪም

ከፊት (ከግራ ወደ ቀኝ)፦ ግዌንደሊን ፓተርሰን፣ ሮበርት ፓተርሰን እና ክሪስቲን አኪን

ታኅሣሥ 2, 2021
ፔሩ

ፔሩ ‘እንደ ጽጌረዳ ያበበችባቸው’ 75 ዓመታት

ፔሩ ‘እንደ ጽጌረዳ ያበበችባቸው’ 75 ዓመታት

በፔሩ እንዲያገለግሉ የተመደቡት የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን ወደ አገሪቱ የደረሱት ጥቅምት 1946 ነው። እነዚህ ሚስዮናውያን ሰፊ የስብከት ክልል ተሰጥቷቸዋል። የ1.3 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ ተሰበጣጥረው ለሚኖሩት ሰባት ሚሊዮን ነዋሪዎች ምሥራቹን መስበክ ነበረባቸው። ላለፉት 75 ዓመታት ሚስዮናውያንና የአገሪቱ አስፋፊዎች በፔሩ ተራራማ አካባቢዎች ባሉ መንደሮችም ሆነ በባሕር ዳርቻ በሚገኙት ከተሞች በትጋት በማገልገል ብዙ ሰዎች እውነትን እንዲማሩ ረድተዋል።

ሚስዮናውያኑ ወደ ፔሩ ተመድበው ከመሄዳቸው በፊት ባሉት ዓመታት በደቡብ አሜሪካ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የፔሩ ዋና ከተማ የሆነችውን ሊማን አልፎ አልፎ በመጎብኘት ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ጽሑፎችን ይሰጡ ነበር። እነዚህ ጉብኝቶች ጥሩ ውጤት አስገኝተዋል። በ1945 በቺሊ የሚያገለግሉ ሁለት ሚስዮናውያን ወደ ሊማ ሄደው በፔሩ የመጀመሪያዎቹን ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች አጠመቁ።

ከጥቅምት 1946 ወዲህ፣ ጊልያድ ገብተው የሠለጠኑ ሚስዮናውያን በፔሩ የስብከቱን ሥራ እንዲያደራጁ ተመደቡ። ፍላጎት ካሳዩ ሰዎች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ያደረጉት በሊማ በሚገኘው የሪማክ አውራጃ ነው። በአገሪቱ የአስፋፊዎችና የሚስዮናውያን ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ የስብከቱ ሥራ ከሊማ አልፎ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መዳረስ ጀመረ። ሥራው በዛሬው ጊዜም መስፋፋቱን ቀጥሏል።

እህት ኔሊና ፑል

በ1946 ወደ ፔሩ ከሄዱት የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን መካከል አንዷ የሆኑት እህት ኔሊና ፑል በመጋቢት 1, 1957 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ በወጣው የሕይወት ታሪካቸው ላይ በፔሩ ስለታየው እድገት ተናግረዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “በአንድ ወቅት ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ የነበሩበት ጠፍ መሬት ‘እንደ ጽጌረዳ ሲያብብ’ ማየት በቃላት ለመግለጽ የሚከብድ ልዩ ስሜት ይፈጥራል።”

የ54ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት ምሩቅ የሆኑትና አሁንም ድረስ በፔሩ እያገለገሉ ያሉት እህት አይሪን ማኒንግስ እንዲህ ብለዋል፦ “እዚህ ከመጣንበት ጊዜ አንስቶ የአስፋፊዎች ቁጥር ከ7,000 ወደ 130,000 ሲያድግ ተመልክተናል። ለዚህ እድገት ጥቂትም ቢሆን አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሌ ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማኛል። ይህ እድገት ሊገኝ የቻለው ይሖዋ ሥራችንን ስለባረከው ነው።”

በአሁኑ ጊዜ በፔሩ እያገለገሉ ያሉት 133,170 አስፋፊዎች የዛሬ 75 ዓመት ለተጣለው መሠረት በጣም አመስጋኝ ናቸው። በፔሩ የተመዘገበው ቲኦክራሲያዊ ታሪክ በኢሳይያስ 60:22 ላይ የሚገኘው ይሖዋ የገባው ቃል እንደተፈጸመ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው፤ ጥቅሱ “ጥቂት የሆነው ሺህ፣ ትንሽ የሆነውም ኃያል ብሔር ይሆናል” ይላል።