ጥር 15, 2020
ፖርቶ ሪኮ
ፖርቶ ሪኮ በኃይለኛ ርዕደ መሬት ተመታች
ጥር 7, 2020 በፖርቶ ሪኮ የደረሰውን 6.4 የተመዘገበ ርዕደ መሬት ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትናንሽ ነውጦች ደርሰው ነበር። ጥር 11 ማለዳ ላይ ደግሞ 5.9 የተመዘገበ ርዕደ መሬት ደሴቲቱን አናውጧታል።
አደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አሁንም የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተቋርጦባቸዋል፤ እንዲሁም ከቤታቸው ውጭ ለመኖር ተገደዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ እንደገለጸው ከወንድሞቻችን መካከል የአካል ጉዳት የደረሰበትም ሆነ ሕይወቱን ያጣ የለም። ይሁንና 248 ወንድሞችና እህቶች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። በተጨማሪም 8 የወንድሞቻችን ቤቶች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን 70 ቤቶች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አሥር የስብሰባ አዳራሾችም ተጎድተዋል። አንድ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የእርዳታ ሥራውን በማደራጀትና ለተጎዱት አስፋፊዎች እረኝነት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ወንድሞቻችን እንዲህ ባለ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነውም መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዴስክ አስተባባሪ የሆነው ወንድም ሮበርት ሄንድሪክስ እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያለው አደጋ በፖርቶ ሪኮ የተለመደ አይደለም፤ ስለዚህ ርዕደ መሬቱ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በጣም አስጨንቋቸዋል። ሆኖም አሁንም አዎንታዊ መሆናቸውን በመመልከታችን በጣም ተበረታተናል። የኤሌክትሪክና የውኃ አቅርቦት ባይኖራቸውም በተቻላቸው መጠን በስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና በአገልግሎት ለመካፈል ጥረት ያደርጋሉ። ሽማግሌዎችም ችግር ላይ ለወደቁ ወንድሞችና እህቶች ማበረታቻና ድጋፍ ለመስጠት የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው።”
ወንድሞቻችን የተፈጥሮ አደጋ ደርሶባቸውም ለመንፈሳዊ ነገሮች የሚያሳዩት አድናቆት ያበረታታናል። ይሖዋ የእእምሮ ሰላም እንዲሰጣቸው እንጸልያለን።—መዝሙር 119:165