ደም መውሰድ—በዘመናችን ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ምን ይላሉ?
የይሖዋ ምሥክሮች ደም ለመውሰድ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው የተነሳ ላለፉት አሥርተ ዓመታት ነቀፋ ሲሰነዘርባቸው ቆይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከደም እንድንርቅ’ የሚሰጠውን ትእዛዝ በማክበር ደም ለመውሰድ ፈቃደኞች አለመሆናቸው ሐኪሞች የታካሚዎቻቸው የተሻለ የሕክምና ምርጫ ሊሆን ይገባዋል ብለው ከሚያምኑት ነገር ጋር የሚጋጭበት ጊዜ አለ።—ሥራ 15:29
ይሁንና ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ተሞክሮ ያካበቱ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ደም መውሰድ የማይጠይቁ ሌሎች የሕክምና አማራጮችን መጠቀም የተሻለ መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ።
በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ተቋም የሚዘጋጀው ስታንፎርድ ሜዲካል ማገዚን የተባለው መጽሔት በ2013 እትሙ ላይ ደምን በተመለከተ አንድ ልዩ ሪፖርት ይዞ የወጣ ሲሆን በመጽሔቱ ላይ ከወጡት ርዕሶች መካከል አንዱ “ከተለመደው አሠራር መውጣት—ደም በመለገስ የሚሰጥ ሕክምና ተፈላጊነቱ እየቀነሰ የመጣው ለምንድን ነው?” የሚል ነበር። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የሆኑት ሣራ ዊልያምስ እንዲህ ብለዋል፦ “ባለፉት አሥርተ ዓመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ጥናቶች እንዳመለከቱት በመላው ዓለም በሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ በቀዶ ጥገና ክፍሎችም ሆነ በሕሙማን ማረፊያ ቦታዎች፣ ደም ታካሚዎቹን ለመርዳት ከሚያስፈልገው በላይ በተደጋጋሚና በብዛት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ፣ በፔንስልቬንያ ሆስፒታል የደም አልባ ሕክምናና ቀዶ ጥገና ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ፓትሪሺያ ፎርድ የሰጡትን ሐሳብ በጽሑፋቸው ውስጥ አካትተዋል። ዶክተር ፎርድ እንዲህ ብለዋል፦ “በሕክምናው ዓለም አንድ ሥር የሰደደ አስተሳሰብ አለ፤ ይኸውም ሰዎች የደማቸው መጠን መሆን አለበት ተብሎ ከሚታሰበው ከቀነሰ ለሞት እንደሚዳረጉና በዚህ ወቅት ሕይወታቸውን ሊያተርፍላቸው የሚችለው ብቸኛ ነገር ደም እንደሆነ ይታሰባል። . . . በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ይህ እውነትነት ሊኖረው ይችል ይሆናል፤ a ይሁን እንጂ በብዙ ሕመምተኞች ላይ እንደሚታየው ከሆነ ይህ እውነት አይደለም።”
የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ደም ያላቸውን አመለካከት ለማወቅ “ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች” በሚለው ሥር የሚገኘውን “ደም የማትወስዱት ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
በየዓመቱ ወደ 700 ለሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሕክምና እርዳታ የሚሰጡት ዶክተር ፎርድ አክለው እንዲህ ብለዋል፦ “ያነጋገርኳቸው አብዛኞቹ ሐኪሞች ብዙውን ጊዜ ታካሚዎች ደም ካልተሰጣቸው በሕይወት መቀጠል አይችሉም የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ አላቸው። . . . እኔም ራሴ በተወሰነ መጠን ይህ እውነት እንደሆነ አምን ነበር። ሆኖም ቀላል የሆኑ የሕክምና ዘዴዎችን ተጠቅሞ እነዚህን ታካሚዎች መርዳት እንደሚቻል መገንዘብ ችያለሁ።”
አርካይቭስ ኦቭ ኢንተርናል ሜድስን የተባለው መጽሔት በነሐሴ 2012 እትሙ ላይ በ28 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአንድ የሕክምና ማዕከል የልብ ቀዶ ሕክምና ባደረጉ ታካሚዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት ያስገኘውን ውጤት ይዞ ወጥቶ ነበር። ውጤቱ እንዳመለከተው የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት ታካሚዎች ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟቸው ደም ከወሰዱት ከሌሎቹ ሕመምተኞች ይልቅ በፍጥነት ማገገም ችለዋል። የይሖዋ ምሥክር የሆኑት ታካሚዎች ደም ከወሰዱት ታካሚዎች ጋር ሲነጻጸሩ ከሕክምናው ጋር የተያያዘ የተወሳሰበ ችግር እምብዛም ያላጋጠማቸው ከመሆኑም ሌላ ከቀዶ ሕክምናው የመትረፍ ዕድላቸው ከሌሎቹ የተሻለ እንደሆነ ታይቷል፤ እንዲሁም ከቀዶ ሕክምናው በኋላ እስከ 20 ዓመት ድረስ በሕይወት የመቀጠል አጋጣሚያቸው ከሌሎቹ ጋር እኩል ሆኖ ተገኝቷል።
ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል በሚያዝያ 8, 2013 እትሙ ላይ ባወጣው አንድ ርዕስ ሥር የሚከተለውን ሐሳብ አስነብቧል፦ “በሃይማኖታዊ አቋማቸው የተነሳ ደም ለመውሰድ ፈቃደኞች ያልሆኑ ታካሚዎች ለብዙ ዓመታት ደም አልባ ቀዶ ጥገና ይኸውም ያለ ደም የሚደረግ ቀዶ ሕክምና ሲደረግላቸው ቆይቷል። . . . አሁን አሁን፣ እንዲህ ያለው የሕክምና ዘዴ በሆስፒታሎች ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ ሄዷል። ደም አልባ ቀዶ ጥገናን የሚደግፉ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ይህ ዓይነቱ ሕክምና ደምን ከመግዛት፣ ከማስቀመጥ፣ ከማጣራት፣ ከመመርመርና ለታካሚው ከመስጠት ጋር የተያያዙ ብዙ ወጪዎችን ይቀንሳል፤ በተጨማሪም ደም ሲለገስ ሊከሰቱ በሚችሉ ኢንፌክሽኖችና ሌሎች ውስብስብ ችግሮች ምክንያት ታካሚዎች ለረጅም ጊዜ በሆስፒታል እንዳይቆዩ ለማድረግ ያስችላል።”
ከዚህ አንጻር የክሊቭላንድ ክሊኒክ የደም ቁጥጥር ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ሮበርት ሎሬንዝ እንዲህ ማለታቸው አያስገርምም፦ “ለአንድ ታካሚ ደም ስትሰጡት ሕመምተኛውን እየረዳችሁት እንዳለ ሆኖ ይሰማችሁ ይሆናል፤ . . . ለረጅም ጊዜ ሲጠናቀሩ የቆዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ግን ሁኔታው ከዚህ ተቃራኒ ነው።”
a የይሖዋ መሥክሮች ደምን በሚመለከት ያላቸውን አቋም ለማወቅ “ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች—ደም የማትወስዱት ለምንድን ነው? የሚለውን ርዕስ ተመልከት።”