ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና
ለልጆቻችሁ አመራር መስጠት የምትችሉት እንዴት ነው?
ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር
በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር በጣም የሚቀራረቡ ሲሆን አመራር ለማግኘት የሚሞክሩትም ከእነሱ ነው። በሌሎች ባሕሎች ግን ልጆች የሚያማክሩት እኩዮቻቸውን ነው።
ልጆች እኩዮቻቸውን ማማከራቸው ለወላጆቻቸው አመራር ያን ያህል ቦታ እንዳይሰጡ ያደርጋቸዋል። ወደ ጉርምስና ዕድሜ ሲደርሱ ደግሞ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ጨርሶ ቁጥጥር እንደሌላቸው ሊሰማቸው ይችላል። ደግሞም ይህ መሆኑ አያስገርምም! ልጆች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከሌሎች ልጆች ጋር ከሆነ የሚያሳድጓቸው ወላጆቻቸው ሳይሆኑ እኩዮቻቸው ይሆናሉ።
ለመሆኑ ልጆች ከወላጆቻቸው ይልቅ እኩዮቻቸውን መቅረብ የሚቀናቸው ለምንድን ነው? አንዳንድ ምክንያቶችን እንመልከት።
ትምህርት ቤት። ልጆች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከእኩዮቻቸው ጋር ስለሚያሳልፉ ከእነሱ ጋር በጣም ሊቀራረቡና ከወላጆቻቸው ይልቅ ለእኩዮቻቸው አመለካከት ትልቅ ቦታ መስጠት ሊጀምሩ ይችላሉ። ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ ሲገቡ ደግሞ ይህ ሁኔታ ይበልጥ ሊባባስ ይችላል።
አብረው ጊዜ አለማሳለፋቸው። በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ ልጆች ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ቤት ውስጥ ማንንም ሰው አያገኙም፤ ምክንያቱም ወላጆቻቸው ሥራ ቦታ ናቸው።
የጉርምስና ዕድሜ። ልጆች ወደ ጉርምስና ዕድሜ ሲደርሱ አለባበሳቸው፣ አነጋገራቸውና አኳኋናቸው ከእኩዮቻቸው ጋር መመሳሰል እንዳለበት ሊሰማቸው ይችላል። ብዙውን ጊዜ ከወላጆቻቸው አመለካከት ይበልጥ የሚያሳስባቸው በእኩዮቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ማግኘታቸው ነው።
የንግዱ ዓለም። የንግዱ ዓለም ለወጣቶች ተብለው ብቻ የተዘጋጁ ቁሳቁሶችንና መዝናኛዎችን ያቀርባል፤ ይህ ደግሞ በልጆችና በወላጆች መካከል ያለውን ክፍተት ይበልጥ ያሰፋዋል። ዶክተር ሮበርት ኤፕስታይን እንደጻፉት “በጉርምስና ዕድሜ ባሉ ልጆች ላይ የሚታየው ባሕል ቢጠፋ በርካታ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች ወዲያውኑ ለኪሳራ ይዳረጋሉ።” a
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ከልጆቻችሁ ጋር ተቀራረቡ።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እኔ ዛሬ የማዝህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ፤ በልጆችህም ውስጥ ቅረጻቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድ ላይ ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሳ ስለ እነሱ ተናገር።”—ዘዳግም 6:6, 7
የልጆቻችሁ እኩዮች ጓደኛ ሊሆኗቸው ቢችሉም የእናንተን ቦታ ሊተኩ አይገባም። ደስ የሚለው ነገር፣ ብዙ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት አብዛኞቹ ልጆችና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ወላጆቻቸውን ያከብሯቸዋል እንዲሁም ሊያስደስቷቸው ይፈልጋሉ። በመሆኑም ከልጆቻችሁ ጋር ከተቀራረባችሁ ከእኩዮቻቸው የበለጠ ተጽዕኖ በእነሱ ላይ ማሳደር ትችላላችሁ።
“ከልጆቻችሁ ጋር ጊዜ ማሳለፍ አለባችሁ፤ ምግብ እንደ ማብሰልና እንደ ጽዳት ያሉ ሥራዎችን አብራችሁ መሥራት ወይም የቤት ሥራቸውን ሲሠሩ አብራችኋቸው መሆን ትችላላችሁ። አንድ ላይ መዝናናት ለምሳሌ ጌም መጫወት እንዲሁም ፊልም ወይም ቴሌቪዥን ማየትም ትችላላችሁ። አልፎ አልፎ ጥቂት ሰዓታት ብቻ አብሮ ማሳለፍ በቂ እንደሆነ ሊሰማችሁ አይገባም። ብዙ ጊዜ አብራችሁ ካላሳለፋችሁ ከልጆቻችሁ ጋር ልትቀራረቡ አትችሉም!”—ሎሬን
ልጆቻችሁ ከእኩዮቻቸው ጋር ብቻ ጓደኛ ሊሆኑ አይገባም።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሞኝነት በልጅ ልብ ውስጥ ታስሯል።”—ምሳሌ 22:15
አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ብዙ ጓደኞች ያላቸው መሆኑ በራሱ በጣም ያስደስታቸዋል። እርግጥ ነው ልጃችሁ ከእኩዮቹ ጋር ጓደኛ መሆኑ ከሌሎች ጋር እንዲግባባ ሊረዳው ይችላል፤ ሆኖም በሳል እንዲሆን ከተፈለገ የተለያየ ዕድሜ ካላቸው ሰዎች ጋር ጓደኛ መሆኑ አስፈላጊ ነው። ደግሞም አንድ ልጅ የሚያስፈልገውን አመራር ከእኩዮቹ ሊያገኝ አይችልም፤ እንዲህ ያለውን አመራር ከማንም በተሻለ መንገድ ሊሰጡ የሚችሉት አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ናቸው።
“የልጃችሁ እኩዮች ስለ አንዳንድ ነገሮች እውቀት ሊኖራቸው ቢችልም ልጃችሁ ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርግ ለመርዳት የሚያስችል የሕይወት ተሞክሮና ጥበብ የላቸውም። ልጆች የወላጆቻቸውን መመሪያ ከተከተሉ ለዕድሜያቸው በሚመጥን መንገድ ማደግና መብሰል ይችላሉ።”—ናድያ
ጥበብ የሚንጸባረቅበት አመራር ስጧቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል።”—ምሳሌ 13:20
ልጆቻችሁ ዕድሜያቸው ከፍ ካለ በኋላም ከእናንተ ጋር ጊዜ ማሳለፋቸው በእጅጉ ይጠቅማቸዋል። ለልጆቻችሁ ጥሩ አርዓያ ሁኗቸው።
“ለልጆች ከሁሉ የተሻለ አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉት ወላጆች ናቸው። ልጆች ወላጆቻቸውን መውደድና ማክበር ከተማሩ ሲያድጉ እንደ እነሱ መሆን ይፈልጋሉ።”—ካትሪን
a ቲን 2.0—ሴቪንግ አወር ችልድረን ኤንድ ፋሚሊስ ፍሮም ዘ ቶርመንት ኦቭ አዶለሰንስ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።