በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ

ልጃችሁን ስለ አልኮል መጠጥ ማስተማር

ልጃችሁን ስለ አልኮል መጠጥ ማስተማር

 “ከልጃችን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ አልኮል መጠጥ ያወራነው ገና የስድስት ዓመት ልጅ ሳለች ነው። የሚገርመው፣ ከጠበቅነው በላይ ብዙ ነገር ታውቅ ነበር።”—አሌክሳንደር

 ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

 ልጆችን ስለ አልኮል መጠጥ ማስተማር በጣም አስፈላጊ ነው። ልጃችሁ አሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እስኪደርስ አትጠብቁ። በሩሲያ የሚኖረው ሃሚት እንዲህ ብሏል፦ “ልጃችንን ገና ከትንሽነቱ አንስቶ ስለ አልኮል መጠጥ አጠቃቀም አስተምረነው ቢሆን ኖሮ በጣም ጥሩ ነበር። ይህ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የተረዳሁት ልጃችን ችግር ውስጥ ከገባ በኋላ ነው። ገና የ13 ዓመት ልጅ ሳለ አዘውትሮ የአልኮል መጠጥ ይጠጣ ነበር።”

 ይህ ጉዳይ ሊያሳስባችሁ የሚገባው ለምንድን ነው?

  •   አብረውት የሚማሩ ልጆች፣ ማስታወቂያዎችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ልጃችሁ ስለ አልኮል መጠጥ ባለው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።

  •   የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል፣ ከዩናይትድ ስቴትስ አጠቃላይ የአልኮል ፍጆታ ውስጥ 11 በመቶ የሚሆነውን የሚጠቀሙት ልጆች እንደሆኑ ገልጿል።

 በእርግጥም የጤና ባለሙያዎች፣ የአልኮል መጠጥ ስላለው አደጋ ልጆችን ከትንሽነታቸው አንስቶ ማስተማር ተገቢ እንደሆነ የሚናገሩት ያለምክንያት አይደለም። ታዲያ ወላጆች እንዲህ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

 ልጃችሁ ምን ጥያቄዎችን ሊያነሳ እንደሚችል አስቀድማችሁ አስቡ። ትናንሽ ልጆች የማወቅ ጉጉት አላቸው፤ ተለቅ ያሉ ልጆች ደግሞ ከትናንሾቹም የበለጠ የማወቅ ጉጉት አላቸው። በመሆኑም ምን ብላችሁ እንደምትመልሱ አስቀድማችሁ መዘጋጀታችሁ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል፦

  •   ልጃችሁ የአልኮል መጠጥ ምን ምን እንደሚል ማወቅ ከፈለገ፣ የወይን ጠጅ ኮምጠጥ ያለ የፍራፍሬ ጭማቂ ጣዕም እንዳለው ቢራ ደግሞ ትንሽ መረር እንደሚል ልትነግሩት ትችላላችሁ።

  •   ልጃችሁ የአልኮል መጠጥ መቅመስ ከፈለገ፣ አልኮል ኃይለኛ ስለሆነ ልጆች ከጠጡት ሰውነታቸውን እንደሚጎዳው ልትነግሩት ትችላላችሁ። የአልኮል መጠጥ መጠጣት ምን ውጤት እንደሚያስከትል ንገሩት፦ አልኮል አንድን ሰው ዘና እንዲል ሊያደርገው ይችላል፤ ከልክ በላይ ከጠጣ ግን ራሱን እንዲያዞረው፣ የሞኝነት ድርጊት እንዲፈጽምና በኋላ ላይ የሚቆጭበትን ነገር እንዲናገር ያደርገዋል።—ምሳሌ 23:29-35

 ራሳችሁን አስተምሩ። መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ ሰው ተግባሩን በእውቀት ያከናውናል” ይላል። (ምሳሌ 13:16) የአልኮል መጠጥ መጠጣት ስለሚያስከትለው ውጤት እንዲሁም በአገራችሁ ከዚህ ጋር በተያያዘ ስላሉት ሕጎችና በሕግ የተከለከሉ ነገሮች ለማወቅ ጥረት አድርጉ። እንዲህ ማድረጋችሁ ልጃችሁን ለመርዳት ዝግጁ እንድትሆኑ ያስችላችኋል።

 ቅድሚያውን ወስዳችሁ በጉዳዩ ላይ ተወያዩ። በብሪታንያ የሚኖር ማርክ የተባለ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ልጆች የአልኮል መጠጥን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ላያውቁ ይችላሉ። የስምንት ዓመት ልጄን ‘አልኮል መጠጣት ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?’ ብዬ ጠየቅኩት። ያናገርኩት ዘና ባለ ሁኔታ ነበር፤ ይህም አመለካከቱን በግልጽ እንዲነግረኝ ረድቶታል።”

 የተለያዩ አጋጣሚዎችን ተጠቅማችሁ ከልጃችሁ ጋር ስለ አልኮል መጠጥ አጠቃቀም የምታወሩ ከሆነ ትምህርቱን በልጃችሁ ልብ ላይ መቅረጽ ቀላል ይሆንላችኋል። ዕድሜውን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ስለ አልኮል መጠጥ የምትሰጡትን ትምህርት እንደ ፆታ ሥነ ምግባር ወይም ራስን ከመኪና አደጋ እንደመጠበቅ ካሉ ሌሎች ጠቃሚ ትምህርቶች ጋር አንድ ላይ ልትሰጡት ትችላላችሁ።

 ጥሩ ምሳሌ ሁኑ። ልጆች ልክ እንደ ስፖንጅ በአካባቢያቸው ያለውን ነገር የመምጠጥ ባሕርይ አላቸው፤ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ደግሞ በልጆች ላይ ከሁሉ የላቀ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት ወላጆች ናቸው። ለመረጋጋት ወይም ጭንቀታችሁን ለማስታገስ ስትሉ ብዙ ጊዜ የአልኮል መጠጥ የምትጠጡ ከሆነ ልጃችሁም በሕይወቱ ውስጥ የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥመው መፍትሔው የአልኮል መጠጥ መጠጣት እንደሆነ ማሰብ ይጀምራል። እንግዲያው ለልጃችሁ ጥሩ ምሳሌ ሁሉ። በቅድሚያ እናንተ ራሳችሁ የአልኮል መጠጥን በአግባቡ ተጠቀሙ።

ከአልኮል መጠጥ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ልጆቻችሁ የእናንተን ምሳሌ ይከተላሉ