ለቤተሰብ
ልጃችሁ የትምህርት ውጤቱን እንዲያሻሽል መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?
ልጃችሁ ስለ ትምህርት ምንም ግድ የሚሰጠው አይመስልም፤ በዚያ ላይ የሚሰጠውን የቤት ሥራ አይሠራም እንዲሁም አያጠናም። በዚህም ምክንያት ውጤቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሽቆልቁሏል፤ ባሕሪውም ቢሆን እየተበላሸ ነው። ታዲያ ልጃችሁ ውጤቱን እንዲያሻሽል መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?
ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር
ልጃችሁን መጫናችሁ ችግሩን ያባብሰዋል። በልጃችሁ ላይ ጫና ማሳደራችሁ ትምህርት ቤትም ሆነ ቤት ውስጥ ሲሆን እንዲጨነቅ ያደርገዋል። ይህም እንዲዋሽ፣ ዝቅተኛ ውጤት ሲያገኝ እንዲደብቀው፣ ሰርተፍኬቱ ላይ ፊርማችሁን አስመስሎ እንዲፈርም ብሎም ከትምህርት ቤት እንዲቀር ሊያደርገው ይችላል። እንዲህ ማድረጉ ደግሞ የባሰ ችግር ያስከትላል።
ሽልማትም ቢሆን የታሰበውን ውጤት ላያስገኝ ይችላል። አንድሩ የተባለ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ሴት ልጃችን ጎበዝ ተማሪ እንድትሆን ለማነሳሳት ስንል ጥሩ ውጤቶች ስታገኝ መሸለም ጀመርን። ሆኖም ይህ ሙሉ ትኩረቷ ሽልማቱ ላይ እንዲሆን አደረጋት። ዝቅተኛ ውጤት ስታመጣ የበለጠ የምታዝነው ጥሩ ውጤት ባለማምጣቷ ሳይሆን ሽልማት ባለማግኘቷ ነበር።”
አስተማሪዎችን መውቀስ ልጃችሁን አይጠቅመውም። አስተማሪዎቹን የምትወቅሱ ከሆነ ልጃችሁ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ጥረት ማድረግ እንደማያስፈልገው ሊያስብ ይችላል። በተጨማሪም ጥፋቱን በሌሎች ላይ እንዲያሳብብና ችግሮቹን ሌሎች እስኪፈቱለት እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ ሊያደርገው ይችላል። በአጭር አነጋገር፣ ልጃችሁ አዋቂ ሲሆን የሚያስፈልገውን በጣም ወሳኝ ችሎታ ይኸውም ለድርጊቶቹ ኃላፊነት የመውሰድን ችሎታ ሳያዳብር ይቀራል።
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ስሜታችሁን ተቆጣጠሩ። በልጃችሁ ውጤት ተናዳችሁ ባላችሁበት ወቅት ከልጃችሁ ጋር ከማውራት ይልቅ ውይይቱን ለሌላ ጊዜ አስተላልፉት። ብራት የተባለ አባት “እኔና ባለቤቴ፣ ስንረጋጋና ራሳችንን በልጆቻችን ቦታ ለማስቀመጥ ስንሞክር የተሻለ ውጤት እናገኛለን” ሲል ተናግሯል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ‘ለመስማት የፈጠናችሁ፣ ለመናገር የዘገያችሁና ለቁጣ የዘገያችሁ ሁኑ።’—ያዕቆብ 1:19
የችግሩን መንስኤ ለይታችሁ እወቁ። አብዛኛውን ጊዜ ልጆች ዝቅተኛ ውጤት እንዲያመጡ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል የሚደርስባቸው ጥቃት፣ ትምህርት ቤት መለወጥ፣ የፈተና ፍርሃት፣ በቤተሰብ ውስጥ ያሉ ችግሮች፣ በቂ እንቅልፍ አለማግኘት፣ በፕሮግራም አለማጥናት እንዲሁም ትኩረት የመሰብሰብ ችግር ይገኙበታል። ልጃችሁ ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገበው ሰነፍ ስለሆነ ነው ብላችሁ ቶሎ አትደምድሙ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንድን ነገር ጠለቅ ብሎ የሚያስተውል ሰው ስኬታማ ይሆናል።”—ምሳሌ 16:20
ለመማር አመቺ ሁኔታዎች እንዲኖሩ አድርጉ። ልጃችሁ የቤት ሥራ የሚሠራበትና የሚያጠናበት ፕሮግራም አውጡ። ልጃችሁ የሚያጠናበት ቦታ ትኩረቱን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ነገሮች (ቴሌቪዥን እና ሞባይል ስልክም ጭምር) የሌሉበት እንዲሆን አድርጉ። ልጃችሁ የቤት ሥራዎቹን ከፋፍሎ እንዲሠራ አድርጉ፤ ይህም ትኩረቱን ሰብስቦ መሥራት እንዲችል ይረዳዋል። በጀርመን የሚኖር ሄክቶር የተባለ አባት “የልጄ ፈተና እየቀረበ ሲሄድ፣ ባለቀ ሰዓት ከመሯሯጥ ይልቅ በየቀኑ የተወሰነ ያህል እንከልሳለን” ሲል ተናግሯል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1
መማር ያለውን ጥቅም አስረዱት። ልጃችሁ መማሩ አሁን የሚያስገኝለትን ጥቅም ይበልጥ በተረዳ መጠን፣ ለመማር የበለጠ ፍላጎቱ ይነሳሳል። ለምሳሌ ያህል፣ ሒሳብ መማሩ ገንዘቡን በጥሩ መንገድ ለመያዝ ይረዳዋል።
ጠቃሚ ምክር፦ ልጃችሁ የቤት ሥራውን ሲሠራ እርዱት እንጂ እናንተ አትሥሩለት። አንድሩ “ልጃችን የጥያቄዎቹን መልሶች ለማግኘት ጥረት ከማድረግ ይልቅ እኛ እንድንነግራት ትጠብቅ ነበር” ሲል ተናግሯል። ልጃችሁ የቤት ሥራውን እንዴት ራሱ መሥራት እንደሚችል አሠልጥኑት።