ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና
ልጆችና ማኅበራዊ ሚዲያ—ክፍል 2፦ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያን በማይጎዳ መንገድ እንዲጠቀም ማሠልጠን
ብዙ ወላጆች ማኅበራዊ ሚዲያ የሚያስከትለው ጉዳት ስለሚያሳስባቸው ልጆቻቸው እንዲጠቀሙ አይፈቅዱላቸውም። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀም ከፈቀዳችሁ ግን ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች እንዲጠበቅና ኢንተርኔትን በአግባቡ እንዲጠቀም ማሠልጠን የምትችሉት እንዴት ነው?
በዚህ ርዕስ ውስጥ፦
ልጃችሁ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች
ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር፦ ማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ የሚሆን ነገር ነው፤ ስለዚህ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም የሚያሳልፈውን ጊዜ ገደብ እንዲያበጅለት የእናንተ እርዳታ ያስፈልገው ይሆናል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም የሚያሳልፈው ጊዜ በቂ እንቅልፍ እንዳያገኝ እንዲሁም ለትምህርቱና ለቤተሰብ ሕይወቱ ትኩረት እንዳይሰጥ እንቅፋት እየሆነበት ነው? ተመራማሪዎች በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች በየቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ መተኛት እንደሚያስፈልጋቸው ይናገራሉ፤ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ረዘም ያለ ሰዓት የሚያሳልፉ ወጣቶች ግን ሰባት ሰዓት እንኳ ላይተኙ ይችላሉ።
ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ልጃችሁን ቅድሚያ ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች አወያዩት፤ ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም የሚያሳልፈው ጊዜ ላይ ገደብ ማበጀቱ ምን ጥቅም እንዳለው ግለጹለት። ምክንያታዊ የሆኑ ገደቦች አውጡለት፤ ለምሳሌ ምሽት ላይ መኝታ ቤት ውስጥ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን መጠቀም እንደማይቻል ልትነግሩት ትችላላችሁ። ዓላማችሁ ልጃችሁ ራስን የመግዛት ባሕርይ እንዲያዳብር መርዳት ነው፤ ይህ ባሕርይ ትልቅ ሰው ሲሆንም በጣም ይጠቅመዋል።—1 ቆሮንቶስ 9:25
የልጃችሁ ስሜታዊ ደህንነት
ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር፦ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ልጃችሁ ማሳመሪያ የተጨማመረባቸውን የሌሎች ፎቶግራፎች ሲመለከት ወይም ጓደኞቹ አስደሳች ነገሮችን ሲያደርግ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ብቻ ሰብስበው የሠሯቸውን ቪዲዮዎች ሲያይ እንደተገለለ ሊሰማውና ጭንቀት ውስጥ ሊገባ ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ቅናትን . . . አስወግዱ።”—1 ጴጥሮስ 2:1
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያ ሲጠቀም ስለ መልክና ቁመናው ከሌሎች ጋር ተገቢ ያልሆነ ንጽጽር ውስጥ ይገባል? ልጃችሁ ሰው ሁሉ አስደሳች ሕይወት እየመራ እንዳለና የእሱ ሕይወት ግን አሰልቺ እንደሆነ ይሰማዋል?
ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ስላለው ጉዳት ልጃችሁን አወያዩት። በዚህ ጉዳይ ይበልጥ የሚቸገሩት ሴቶች ልጆች ናቸው፤ ምክንያቱም ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነትና የመልካቸው ጉዳይ ከወንዶች ልጆች ይበልጥ ያሳስባቸዋል። ልጃችሁ አልፎ አልፎ ከማኅበራዊ ሚዲያ እረፍት እንዲወስድም ሐሳብ ልታቀርቡለት ትችላላችሁ። ጄከብ የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “የማኅበራዊ ሚዲያ አፕሊኬሽኑን ለተወሰነ ጊዜ አጥፍቼው ነበር። ይህን ማድረጌ ቅድሚያ ልሰጣቸው በሚገባኝ ነገሮች እንዲሁም ስለ ራሴም ሆነ ስለ ሌሎች ባለኝ አመለካከት ላይ ለውጥ እንዳደርግ ረድቶኛል።”
የልጃችሁ የኢንተርኔት ጠባይ
ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር፦ ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም ከብዙ ሰው ጋር አብሮ እንደ መኖር እንደሆነ ሲገለጽ ይሰማል። እያንዳንዱን እንቅስቃሴያችንን ሁሉም ሰው ስለሚያየው አለመግባባትና ግጭት በቀላሉ ሊፈጠር ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ . . . ከእናንተ መካከል ይወገድ። ይልቁንም አንዳችሁ ለሌላው ደጎች . . . ሁኑ።”—ኤፌሶን 4:31, 32
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያ ሲጠቀም ሌሎችን ማማት ወይም ደግነት የጎደለው ነገር መናገር አሊያም ከሰዎች ጋር መጋጨት ጀምሯል?
ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ልጃችሁ ኢንተርኔት ሲጠቀም ጥሩ ጠባይ እንዲኖረው አሠልጥኑት። ዲጂታል ኪድስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ወላጆች ልጆቻችንን በአካልም ሆነ በኢንተርኔት የሚያገኟቸውን ሰዎች የሚጎዳ ነገር ማድረግ ስህተት እንደሆነ የማሠልጠን ኃላፊነት አለብን።”
ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም ለሕይወት የግድ አስፈላጊ ነገር አይደለም፤ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆቻቸው ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀሙ የሚፈቅዱት ሁሉም ወላጆች እንዳልሆኑም አስታውሱ። ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀም የምትፈቅዱ ከሆነ ግን በሚጠቀምበት ሰዓት ላይ ገደብ ለማበጀት፣ ጥሩ ጓደኞች ለመምረጥና ከመጥፎ ነገሮች ለመራቅ የሚያስፈልገው ብስለት እንዳለው እርግጠኞች መሆን ይኖርባችኋል።