በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | ትዳር

የአልኮል መጠጥን ከልክ በላይ መጠጣት በትዳር ውስጥ የሚፈጥረው ችግር

የአልኮል መጠጥን ከልክ በላይ መጠጣት በትዳር ውስጥ የሚፈጥረው ችግር

 የትዳር ጓደኛህ የመጠጥ ልማድህ እንዳሳሰባት ነግራህ ታውቃለች? ከሆነ ልታስብባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች አሉ። a

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 ትዳርና የአልኮል መጠጥን ከልክ በላይ መጠጣት—አደገኛ ጥምረት

 የአልኮል መጠጥን ከልክ በላይ መጠጣት የልብ ሕመምን፣ የጉበት በሽታንና ካንሰርን ጨምሮ ብዙ የጤና ችግሮች ሊያስከትል ይችላል። ሆኖም ከልክ በላይ መጠጣት ጉዳት የሚያደርሰው በጤና ላይ ብቻ አይደለም፤ በትዳርም ውስጥ ብዙ ችግሮችን ያስከትላል። ከልክ በላይ የሚጠጣ ሰው ቤተሰቡን ለገንዘብ ችግር ሊዳርግ፣ በቤተሰቡ ላይ አካላዊ ጥቃት ሊፈጽም፣ ታማኝነቱን ሊያጓድል እንዲሁም ወደ ፍቺ ሊያመራ ይችላል።

 መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ መጠጣት ስለሚያስከትለው ጉዳት ሲገልጽ “እንደ እባብ ይናደፋልና፤ እንደ እፉኝትም መርዙን ይረጫል” ይላል። (ምሳሌ 23:32) ታዲያ አንተ የአልኮል መጠጥ ጥገኛ መሆን አለመሆንህን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

 የአልኮል መጠጥ ጥገኛ ሆነሃል?

 የሚከተሉት ጥያቄዎች ይህን ለማወቅ ሊረዱህ ይችላሉ፦

  •   የምትጠጣውን መጠን ለመቆጣጠር ትቸገራለህ?

  •   ቀጥሎ የምትጠጣበት ጊዜ ይናፍቅሃል?

  •   የመጠጥ ልማድህ ትዳርህን ጨምሮ በሕይወትህ ውስጥ ችግር እያስከተለ እንዳለ እያወቅክም ትጠጣለህ?

  •   ለማቆም ስትሞክር ደስ የማይል ስሜት ይሰማሃል?

  •   በመጠጥ ልማድህ የተነሳ ከትዳር ጓደኛህ ጋር ትጨቃጨቃለህ?

  •   ከበፊቱ የበለጠ ብትጠጣም ምንም እንደማይልህ እያስተዋልክ መጥተሃል?

  •   በቤትህ ወይም በሥራ ቦታህ ተደብቀህ ትጠጣለህ?

 ከእነዚህ ጥያቄዎች ለአንዱ ወይም ከዚያ በላይ ለሆኑት ‘አዎ’ የሚል መልስ ከሰጠህ የአልኮል መጠጥ ጥገኛ ሆነህ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም የአልኮል መጠጥ ሱስ ይኖርብህ ይሆናል።

 ችግሩን አምነህ ላለመቀበል ሰበብ አታቅርብ

 የትዳር ጓደኛህ የመጠጥ ልማድህ እንዳሳሰባት ነግራህ ታውቃለች? ከሆነ ችግሩን ለማቃለል ወይም ያን ያህል አሳሳቢ እንዳልሆነ ለማሳመን ሞክረህ ይሆናል። እንደሚከተሉት ያሉ ሐሳቦችን በመናገር የትዳር ጓደኛህን ጨምሮ ሌሎችን ለችግሩ ተጠያቂ ለማድረግ ሞክረህ ሊሆን ይችላል፦

  •   “በትዳሬ ደስተኛ ብሆን ኖሮ ወደ መጠጥ ዞር ባላልኩ ነበር።”

  •   “እንደ እኔ አለቃ ያለ አለቃ ቢያጋጥምሽ አንቺም መጠጣትሽ አይቀርም።”

  •   “ከእኔ በላይ የሚጠጣ ስንት ሰው አለ።”

 እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን መናገርህ የአልኮል መጠጥ ከትዳርህ እንደበለጠብህ የሚያሳይ ይሆን? የበለጠ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው የትኛው ነው?

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ያገባ ሰው . . . ሚስቱን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደሚችል [ያስባል]።”​—1 ቆሮንቶስ 7:33

ችግሩን አምኖ አለመቀበል በአንተና በትዳር ጓደኛህ መካከል ግንብ እንደ መገንባት ነው፤ የተሻለ የሚሆነው ግንቡን በመስኮት በመተካት የትዳር ጓደኛህ ያሳሰባትን ነገር ለማየት መሞከር ነው።

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

  •   የትዳር ጓደኛህን ሐሳብ በቁም ነገር ተመልከተው። የትዳር ጓደኛህ ጉዳዩን አጋንና እንዳየችው ቢሰማህም እንኳ ማስተካከያ ብታደርግ ምን ችግር አለው? እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆንክ፣ ማለትም ጉዳዩ የትዳር ጓደኛህን እንደሚያስጨንቃት እያወቅክም የመጠጥ ልማድህን ለማስተካከል አሻፈረኝ ካልክ ይህ በራሱ ለአልኮል መጠጥ የምትሰጠው ቦታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።”​—1 ቆሮንቶስ 10:24

  •   በቂ መረጃ ይኑርህ። አንድ ወታደር በውጊያ ድል ለማድረግ ጠላቱ የሚጠቀምበትን ስልት ማወቅ ያስፈልገዋል። የአንተም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፦ ጠላትህን ለማሸነፍ ስለ አልኮል ሱስና ይህ ችግር ሰዎችን ስለሚያጠምድበት መንገድ ትክክለኛ ግንዛቤ ሊኖርህ ይገባል። በተጨማሪም በሆነ መልኩ የአልኮል ጥገኝነት ችግር እንዳለብህ ካስተዋልክ ከዚህ ችግር ለመላቀቅና ድጋሚ እንዳያገረሽብህ ለመከላከል ስለሚረዱህ ውጤታማ ዘዴዎች ማወቅ ይኖርብሃል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እናንተን ከሚዋጉት ሥጋዊ ፍላጎቶች ምንጊዜም እንድትርቁ አሳስባችኋለሁ።”​—1 ጴጥሮስ 2:11

  •   እርዳታ ለማግኘት ሞክር። የማገገሚያ ተቋማትን፣ የሕክምና ጣቢያዎችንና ሆስፒታሎችን ጨምሮ በአልኮል ሱስ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ የተለያዩ የጤና እንክብካቤ ማዕከላት አሉ። በተጨማሪም የጎለመሰ ጓደኛህን እርዳታ ልትጠይቅ ትችላለህ፤ ጓደኛህ ለአልኮል ጥገኝነትህ አስተዋጽኦ ያደረጉ መሠረታዊ ችግሮችን ለይተህ እንድታውቅ ሊረዳህ ይችላል። ወደ ቀድሞው ልማድህ ለመመለስ ስትፈተንም የእሱን እርዳታ ጠይቅ።

    በዘርፉ የሠለጠነን የሕክምና ባለሙያ እርዳታ ብታገኝ የተሻለ ይሆን?

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”​—ምሳሌ 17:17

 የአልኮል መጠጥ ሱስ ውስብስብ ችግር ከመሆኑ አንጻር ይህን በተመለከተ የተጻፈን አንድ አጭር ርዕሰ ጉዳይ በማንበብ ወይም እንዲሁ “ለመቀነስ እሞክራለሁ” በማለት ብቻ ሊፈታ የሚችል አይደለም። ሆኖም ይህን ጉዳይ የምትይዝበት መንገድ ከጤንነትህ ባለፈ ትዳርህን ጭምር ሊነካ እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብሃል።

 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት፦ ሌሎች የአልኮል መጠጥ ሱስን ማሸነፍ ስለቻሉበት መንገድ የሚገልጹትን የሚከተሉትን ርዕሶች አንብብ።

 አሁን ጨካኝ ሰው አይደለሁም

 አሁን በራሴ አላፍርም

 የምኖረው ጎዳና ላይ ነበር

 በተጨማሪም ‘በሕይወቴ ተመረርኩ’ የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል ይህ ርዕስ የተዘጋጀው ከባሎች አንጻር ቢሆንም ሐሳቦቹ ለባሎችም ለሚስቶችም ይሠራሉ።