ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና
ንባብ ለልጆች አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?—ክፍል 1፦ ማንበብ ወይስ ማየት?
ልጆቻችሁ አረፍ ሲሉ ማድረግ የሚመርጡት ምንድን ነው? ቪዲዮ ማየት ወይስ ማንበብ? ብዙውን ጊዜ ይዘው የሚታዩት ምንድን ነው? ዘመናዊ ስልክ ወይስ መጽሐፍ?
ንባብ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ተቀናቃኞች ገጥመውታል፤ ቴሌቪዥንና ኢንተርኔት ላይ የሚታዩ ነገሮች ሰዎች ንባብን ቸል እንዲሉ እያደረጓቸው ነው። ጄን ሂሊ በ1990 የጻፈችው ኢንዴንጀርድ ማይንድስ የተሰኘው መጽሐፍ “ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ንባብ ከናካቴው ሊጠፋ ይችላል” ይላል።
መጽሐፉ በተጻፈበት ወቅት ይህ ሐሳብ ትንሽ የተጋነነ ሊመስል ይችላል። መጽሐፉ ከተጻፈ ከሠላሳ ዓመታት በኋላ ማለትም አሁን ግን ቴክኖሎጂ በጣም በተስፋፋባቸው አገሮች የሚኖሩ አስተማሪዎች፣ በጥቅሉ ሲታይ የወጣቶች የንባብ ችሎታ እንዳሽቆለቆለ ይገልጻሉ።
በዚህ ርዕስ ውስጥ
ንባብ ለልጆች አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ንባብ በዓይነ ሕሊና የመሣል ችሎታን ያሳድጋል። ለምሳሌ አንድ ታሪክ ስታነብቡ የገጸ ባሕርያቱ ድምፅ ምን ዓይነት ነው? መልካቸው ምን ይመስላል? አካባቢውስ ምን ዓይነት ነው? ደራሲው አንዳንድ ፍንጮችን ይሰጠን ይሆናል። የቀረውን የሚሞላው ግን አንባቢው ራሱ ነው።
ሎራ የተባለች አንዲት እናት እንዲህ ብላለች፦ “ቪዲዮ ስንመለከት፣ የምናየው ሌላ ሰው በዓይነ ሕሊናው የሣለውን ነገር ነው። ይህ በራሱ አስደሳች ቢሆንም ማንበብ ግን ለየት ያለ ስሜት ይፈጥራል፤ ስናነብ በጽሑፍ የሰፈረውን ሐሳብ አእምሯችን ሕይወት ይዘራበታል።”
ንባብ መልካም ባሕርያትን ለማዳበር ይረዳል። ልጆች ሲያነብቡ የማገናዘብና ችግሮችን የመፍታት ችሎታቸው ይዳብራል። በተጨማሪም ልጆች ለማንበብ ትኩረታቸውን መሰብሰብ ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው እንደ ትዕግሥት፣ ራስን መግዛትና የሌሎችን ስሜት መረዳት ያሉ ባሕርያትን ለማዳበር ይረዳቸዋል።
ንባብ በእርግጥ የሌሎችን ስሜት የመረዳት ችሎታን ለማዳበር ይረዳል? አዎ። አንዳንድ ምሑራን እንደገለጹት ልጆች አንድን ታሪክ ቀስ ብለው በጥሞና ማንበባቸው ስለ ገጸ ባሕርያቱ ስሜት ለማሰብ ይረዳቸዋል። ይህ ደግሞ በእውነታው ዓለም የሚያገኟቸውንም ሰዎች ስሜት ለመረዳት ሊያግዛቸው ይችላል።
ንባብ በጥልቀት የማሰብ ችሎታን ያዳብራል። አንድ ሰው በሚያነብበት ጊዜ፣ ደራሲው ሐሳቡን ያዋቀረበትን መንገድ ለመረዳት ቀስ ብሎ ማንበብ ይችላል፤ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም መለስ ብሎ ያነበበውን ነገር ይከልሳል። እንዲህ ማድረጉ ያነበበውን ነገር ለማስታወስና ከትምህርቱ ጥቅም ለማግኘት ይረዳዋል።—1 ጢሞቴዎስ 4:15
ጆሴፍ የተባለ አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “በምናነብበት ጊዜ የአንድን አገላለጽ ትርጉም በጥሞና ማሰብ፣ ከምናውቀው ነገር ጋር ማገናኘት እንዲሁም ከሐሳቡ ትምህርት ለማግኘት መሞከር እንችላለን። ቪዲዮ በምናይበት ጊዜ ግን በዚህ መልኩ በጥልቀት ማሰብ ብዙውን ጊዜ ቀላል አይደለም።”
ዋናው ነጥብ፦ ቪዲዮዎችና ሌሎች የሚታዩ ነገሮች የራሳቸው ጥቅም ቢኖራቸውም ልጆቻችሁ ለንባብ ጊዜ የማይመድቡ ከሆነ ብዙ ነገር ሊቀርባቸው ይችላል።
ልጆች የንባብ ልማድ እንዲያዳብሩ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?
በተቻለ ፍጥነት ጀምሩ። የሁለት ወንዶች ልጆች እናት የሆነችው ክሎዊ እንዲህ ብላለች፦ “ልጆቻችን ገና ከመወለዳቸው በፊትም እናነብላቸው ነበር፤ ከተወለዱ በኋላም በዚህ ልማዳችን ቀጠልን። ያደረግነው ጥረት ክሶናል። ከጊዜ በኋላ ልጆቻችን የንባብ ልማድ አዳበሩ፤ እንዲያውም ንባብ መዝናኛቸው ሆነ።”
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ቅዱሳን [መጻሕፍትን] ከጨቅላነትህ ጀምሮ አውቀሃል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:15
ለንባብ አመቺ ሁኔታ ፍጠሩ። ቤታችሁ ውስጥ ብዙ የሚነበብ ነገር እንዲኖር በማድረግ የልጆቻችሁ የንባብ ፍላጎት እንዲነሳሳ አድርጉ። የአራት ልጆች እናት የሆነችው ታማራ “ልጃችሁ የሚወዳቸውን ዓይነት መጻሕፍት ፈልጋችሁ አልጋው አጠገብ አስቀምጡለት” የሚል ሐሳብ ሰጥታለች።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልጅን ሊሄድበት በሚገባው መንገድ አሠልጥነው፤ በሚያረጅበት ጊዜም እንኳ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።”—ምሳሌ 22:6
የልጆቻችሁን የኢንተርኔት አጠቃቀም ገድቡ። ዳንኤል የተባለ አንድ አባት ከኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ነፃ የሆነ ምሽት መመደብ ጠቃሚ እንደሆነ ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “በሳምንት ውስጥ ቢያንስ አንዱን ምሽት ቴሌቪዥን ሳንከፍት ለማሳለፍ ወስነን ነበር። በዚያ ምሽት አብረን ሆነን ወይም ለየብቻችን መጽሐፍ እናነብባለን።”
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10
ጥሩ ምሳሌ ሁኑ። የሁለት ሴቶች ልጆች እናት የሆነችው ካሪና እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥታለች፦ “ለልጆቻችሁ ታሪኩ ሕያው እንዲሆን በሚያደርግ መንገድ እንዲሁም በጉጉት አንብቡላቸው። እናንተ ማንበብ የምትወዱ ከሆነ ልጆቻችሁም ምሳሌያችሁን ሊከተሉ ይችላሉ።”
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለሰዎች ለማንበብ . . . የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።”—1 ጢሞቴዎስ 4:13
ሁሉም ልጆች ለንባብ ከፍተኛ ፍቅር ያዳብራሉ ማለት አይደለም። ሆኖም የእናንተ ማበረታቻ ልጆቻችሁ የማንበብ ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ሊረዳቸው ይችላል። የሁለት ሴቶች ልጆች አባት የሆነው ዴቪድ ከዚህም ያለፈ ነገር አድርጓል። እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቼ የሚያነብቡትን ነገር አነብብ ነበር። ይህም ስለ ፍላጎታቸው እንዳውቅ እንዲሁም ከእነሱ ጋር የማወራው ነገር እንዳገኝ ረድቶኛል። የራሳችን የንባብ ክበብ ነበረን ሊባል ይችላል። በጣም ደስ ይል ነበር!”