ለቤተሰብ | ትዳር
የሚያበሳጫችሁን ጠባይ በአዎንታዊ መንገድ ማየት
አንዳችሁ ያለዕቅድ አዳዲስ ነገሮችን ማድረግ ትወዱ ይሆናል፤ ሌላኛችሁ ደግሞ ሁሉንም ነገር አስቀድማችሁ ማቀድ ልትፈልጉ ትችላላችሁ።
አንዳችሁ ዝምተኛና ቁጥብ ትሆኑ ይሆናል፤ ሌላኛችሁ ደግሞ በጣም ተግባቢና ከሌሎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚያስደስታችሁ ልትሆኑ ትችላላችሁ።
የትዳር ጓደኛችሁ ያሉት አንዳንድ ጠባዮች ያበሳጯችኋል? በእነዚህ ጠባዮች ላይ ማተኮራችሁ ትዳራችሁን ሊጎዳው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስም “አንድን ጉዳይ ደጋግሞ የሚያወራ . . . የልብ ጓደኛሞችን ይለያያል” ይላል።—ምሳሌ 17:9
የትዳር ጓደኛችሁ ያለው የሚያበሳጭ ጠባይ በመካከላችሁ ግጭት እንዲፈጥር ከመፍቀድ ይልቅ እንዲህ ያለውን ጠባይ በአዎንታዊ መንገድ ለማየት ልትሞክሩ ትችላላችሁ።
በዚህ ርዕስ ውስጥ፦
የሚያበሳጫችሁን ጠባይ በአዎንታዊ መንገድ ማየት
የትዳር ጓደኛችሁ ያለው የሚያበሳጭ ጠባይ ከምትወዱለት ባሕርይ ጋር ተዛማጅነት ሊኖረው ይችላል። እስቲ ሦስት ምሳሌዎችን እንመልከት፦
“ባለቤቴ አንዳንድ ነገሮችን የሚያከናውነው ወይም ከቤት ለመውጣት የሚዘገጃጀው ቀስ ብሎ ነው። ሆኖም ይህ ጠባዩ ታጋሽ እንዲሆን ያደርገዋል፤ እኔንም የሚይዘኝ በትዕግሥት ነው። ነገሮችን ቀስ ብሎ ማከናወኑ አንዳንድ ጊዜ ቢያበሳጨኝም የምወድለት ባሕርይም ከእሱ ጋር የተያያዘ ነው።”—ቼልሲ
“ባለቤቴ ሁሉንም ነገር በዝርዝር ማቀድ ትወዳለች፤ ሁሉም ነገር በዕቅዷ መሠረት እንዲሄድ ትፈልጋለች፤ ይህ ደግሞ አንዳንዴ ያበሳጫል። በሌላ በኩል ግን ለዝርዝር ጉዳዮች ትኩረት የምትሰጥ መሆኑ ምንጊዜም ዝግጁ እንድትሆን ያስችላታል።”—ክሪስቶፈር
“ባለቤቴ በአንዳንድ ነገሮች ረገድ ግድየለሽ ነው፤ ይህ ደግሞ ያበሳጫል። በሌላ በኩል ግን መጀመሪያም እንድወደው ያደረገኝ አንዱ ነገር የማይጨናነቅ መሆኑ ነው። ውጥረት በሚፈጥሩ ሁኔታዎች ውስጥ መረጋጋት መቻሉ ያስደንቀኛል።”—ዳኒዬል
ቼልሲ፣ ክሪስቶፈር እና ዳኒዬል እንደተገነዘቡት ብዙውን ጊዜ፣ የትዳር ጓደኛችን ያሉት ድክመቶችና ጠንካራ ጎኖች የአንድ ባሕርይ የተለያዩ ገጽታዎች ናቸው። የአንድን ሳንቲም አንድ ገጽታ ለይቶ ማስወገድ እንደማይቻል ሁሉ የትዳር ጓደኛችሁን ደካማ ጎን ከጠንካራ ጎኑ ለይታችሁ ማስወገድ አትችሉም።
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጠባዮች አዎንታዊ ጎን የላቸውም። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ሰዎች ‘በቀላሉ የሚቆጡ’ እንደሆኑ ይናገራል። (ምሳሌ 29:22) አንድ ሰው እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ካለው ‘የመረረ ጥላቻን፣ ቁጣን፣ ንዴትን፣ ጩኸትንና ስድብን ሁሉ ለማስወገድ’ የቻለውን ሁሉ ማድረግ አለበት። a—ኤፌሶን 4:31
ይሁንና አንድ ጠባይ በራሱ ያን ያህል መጥፎ ባይሆንም የሚያበሳጫችሁ ከሆነ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁን . . . ቀጥሉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተከተሉ።—ቆላስይስ 3:13
በተጨማሪም፣ የሚያበሳጫችሁ ጠባይ ያለውን አዎንታዊ ጎን ለማየት ሞክሩ፤ ምናልባትም መጀመሪያውኑ የትዳር ጓደኛችሁን እንድትወዱት ያደረጋችሁ ይህ ባሕርይ ሊሆን ይችላል። ጆሴፍ የተባለ አንድ ባለትዳር እንዲህ ብሏል፦ “በሚያበሳጨን ጠባይ ላይ ማተኮር የአንድን አልማዝ ውበት ከማድነቅ ይልቅ በሹል ጠርዙ ላይ እንደማተኮር ነው።”
መወያያ ሐሳብ
በመጀመሪያ፣ ቀጥሎ የቀረቡትን ጥያቄዎች በየግላችሁ ለመመለስ ሞክሩ። ከዚያም መልሳችሁን ተወያዩበት።
የትዳር ጓደኛችሁ ያለው አንድ ጠባይ በትዳራችሁ ውስጥ ችግር እየፈጠረ እንዳለ ይሰማችኋል? ከሆነ ይህ ጠባይ ምንድን ነው?
ይህ ጠባይ በእርግጥ ትልቅ ችግር ነው? ወይስ ያን ያህል መጥፎ ባይሆንም እንዲሁ ያበሳጫችኋል?
ይህ ጠባይ አዎንታዊ ገጽታ አለው? ከሆነ ይህ ገጽታ ምንድን ነው? የትዳር ጓደኛችሁ ያለውን ይህን ባሕርይ የምታደንቁትስ ለምንድን ነው?
a “ቁጣን መቆጣጠር የሚቻለው እንዴት ነው?” “ጎጂ ንግግርን ማስወገድ የሚቻለው እንዴት ነው?” እና “መጨቃጨቅ ማቆም የምትችሉት እንዴት ነው?” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከቱ።