ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና
ልጄ ቤት ውስጥ ቁጭ ማለት ቢሰለቸውስ?
ልጃችሁ ቤት ውስጥ መቀመጥ ስልችት ብሎታል። “በጣም ደብሮኛል!” ይላችኋል። ቴሌቪዥኑን ከመክፈታችሁ ወይም “የምትወደውን የቪዲዮ ጌም ተጫወት” ከማለታችሁ በፊት የሚከተሉትን ነጥቦች አስቡባቸው።
የተሰላቹ ልጆች—አንዳንድ ወላጆች ያስተዋሉት ነገር
በመዝናናት የሚያሳልፉት ጊዜና የመዝናኛው ዓይነት ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል። ሮበርት የተባለ አባት እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ልጆች የዕለት ተዕለት ሕይወት፣ ቴሌቪዥን ከማየት ወይም የቪዲዮ ጌም ከመጫወት አንጻር ሲታይ አሰልቺ ይሆንባቸዋል። የተለመዱ እንቅስቃሴዎች ያን ያህል አያስደስቷቸውም።”
ባለቤቱ ባርባራም በዚህ ሐሳብ ትስማማለች። እንዲህ ብላለች፦ “በእውነታው ዓለም ላይ የምናደርጋቸው ነገሮች ማሰብና መድከም ይጠይቃሉ፤ በአብዛኛው ደግሞ ውጤታቸው የሚታየው ቀስ በቀስ ነው። ብዙ ጊዜያቸውን ቴሌቪዥን በማየት ወይም የቪዲዮ ጌም በመጫወት ለሚያሳልፉ ልጆች ደግሞ ይህ አሰልቺ ይሆንባቸዋል።”
ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመቃኘት ጊዜ ማሳለፍ ልጆች ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅ እንዲል ሊያደርግ ይችላል። አንድ ልጅ ጓደኞቹ የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች ሲመለከት የእሱ ሕይወት አሰልቺ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። ቤት የተባለች ልጅ “‘ሁሉም ሰው ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ነው፤ ቤት ውስጥ የተጎለትኩት እኔ ብቻ ነኝ’ ብለህ ልታስብ ትችላለህ” ብላለች።
በተጨማሪም አንድ ሰው ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመቃኘት በርካታ ሰዓታትን የሚያሳልፍ ከሆነ የባዶነት ስሜት ሊሰማው ይችላል፤ ድብርቱም ቢሆን አይጠፋም። ክሪስ የተባለ ወጣት “ጊዜህን ሊይዝልህ ይችላል፤ ስትጨርስ ግን ምንም የሠራኸው ቁም ነገር የለም” በማለት ተናግሯል።
ድብርት ጥሩ አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል። ካትሪን የተባለች እናት፣ ድብርት ልጆች አዳዲስ ነገሮችን የሚሠሩበት አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ ‘አንድን ተራ ካርቶን እንደ መኪና፣ ጀልባ ወይም መንኮራኩር አድርገው ሊያስቡት ይችላሉ። ሶፋውን ብርድ ልብስ በማልበስ ደግሞ ድንኳን ሊሠሩ ይችላሉ።’
በእርግጥም፣ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ሼሪ ተርክል ድብርትን “ምናባችን የሚያሰማው ጥሪ” በማለት መግለጻቸው ተገቢ ነው። a በመሆኑም ይህ ስሜት በራሱ መጥፎ እንደሆነ ተደርጎ ሊታሰብ አይገባም። እንዲያውም ዲስኮኔክትድ የተባለው መጽሐፍ “ድብርት በአእምሯችን ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ፣ ክብደት ማንሳት በጡንቻዎቻችን ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ጋር ይመሳሰላል” ብሏል።
ዋናው ነጥብ፦ ልጆቻችሁ ድብርት ሲሰማቸው ሁኔታውን እንደ ችግር ሳይሆን አዲስ ነገር እንዲፈጥሩ ልትረዷቸው እንደምትችሉበት አጋጣሚ አድርጋችሁ ተመልከቱት።
የተሰላቹ ልጆች—ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ሁኔታው የሚፈቅድላችሁ ከሆነ ልጆቻችሁ ከቤት ውጭ እንዲጫወቱ አድርጉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ባርባራ እንዲህ ብላለች፦ “የፀሐይ ብርሃንና ንጹሕ አየር በድብርት ስሜት ላይ የሚያመጣው ለውጥ አስገራሚ ነው። ልጆቻችን ከቤት ውጭ መጫወት ከጀመሩ በኋላ፣ በምናብ የመሣል ችሎታቸው በጣም ጨምሯል።”
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ . . . ለመሳቅ [እና] ለመፈንጨትም ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1, 4 የግርጌ ማስታወሻ
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጆቼ ከቤት ውጭ መጫወት የሚችሉበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? ከቤት ውጭ እንዲጫወቱ ማድረግ የማይቻል ከሆነ ቤት ውስጥ አዳዲስ ነገሮችን እንዲሠሩ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
ልጆቻችሁ ሌሎችን የሚጠቅም ነገር እንዲያደርጉ እርዷቸው። ሊሊያን የተባለች እናት እንዲህ ብላለች፦ “በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ግቢ እንዲያጸዱ ወይም ምግብ አብስለው በመውሰድ እንዲጠይቋቸው አድርጉ። ሌሎችን የሚጠቅም ነገር መሥራት እውነተኛ ደስታ ያስገኛል።”
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለጋስ ሰው ይበለጽጋል፤ ሌሎችን የሚያረካም እሱ ራሱ ይረካል።”—ምሳሌ 11:25
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጆቻችሁ ሌሎችን የሚጠቅም ነገር በማድረግ ደስታ እንዲያገኙ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?
ጥሩ ምሳሌ ሁኑ። ስለ ውሏችሁ የምታወሩበት መንገድ በልጆቻችሁ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሣራ የተባለች እናት እንዲህ ብላለች፦ “ሕይወታችን አሰልቺ እንደሆነ በሚያስመስል መንገድ የምናወራ ከሆነ ልጆቻችንም ይህንኑ ይማራሉ። ንግግራችን አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ያተኮረ ከሆነ ግን ልጆቻችንም የእኛን ምሳሌ ይከተላሉ።”
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ደስተኛ ልብ ያለው ሰው . . . ሁልጊዜ ግብዣ ላይ ያለ ያህል ነው።”—ምሳሌ 15:15
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ተደጋጋሚ ስለሆኑ እንቅስቃሴዎች የማወራበት መንገድ ለልጆቼ ምን መልእክት ያስተላልፋል? ልጆቼ የድብርት ስሜት ሲሰማኝ የማደርገውን ነገር አይተው ምን ይማራሉ?
ጠቃሚ ምክር፦ ልጆቻችሁ ማድረግ የሚፈልጓቸውን ነገሮች ዝርዝር እንዲጽፉ አድርጉ። አሊሰን የተባለች እናት “እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የመጡለትን አዳዲስ ሐሳቦች የሚያስገባበት የሐሳብ መስጫ ሣጥን አለን” ብላለች።
a ሪክሌይሚንግ ኮንቨርሴሽን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።