ለቤተሰብ
የአመለካከት ልዩነትን ማስታረቅ
ባለትዳሮች የፍላጎት፣ የልማድ ወይም የባሕርይ ልዩነት ያላቸው መሆኑ ትዳራቸውን ተፈታታኝ ሊያደርግባቸው ይችላል። ሆኖም እንደሚከተሉት ባሉ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን የአመለካከት ልዩነት ማስታረቅ ይበልጥ ፈታኝ እንደሚሆን ግልጽ ነው፦
ከዘመዶቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ርዝመት
የገንዘብ አያያዝ
ልጆች ለመውለድ መወሰን
አንተና ባለቤትህ የአመለካከት ልዩነት ካጋጠማችሁ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር
አንድ ዓይነት መሆን አይጠበቅባችሁም። በጣም የሚጣጣሙ ባለትዳሮችም እንኳ የአመለካከት ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል፤ እንዲያውም በጣም ከባድ በሚባሉ ጉዳዮችም ጭምር አመለካከታቸው ሊለያይ ይችላል።
“ያደግኩት በጣም በሚቀራረብ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ቅዳሜና እሁድ ከአያቶቻችን እንዲሁም ከአጎቶቻችን፣ ከአክስቶቻችንና ከልጆቻቸው ጋር ጊዜ እናሳልፍ ነበር። የባሌ ቤተሰቦች ግን ያን ያህል አይቀራረቡም። ስለዚህ ቤተሰቦቻችንን ለመጠየቅ ወይም ርቀው ከሚኖሩ ዘመዶቻችን ጋር ለመነጋገር ምን ያህል ጊዜ መመደብ አለብን በሚለው ጉዳይ ላይ ያለን አመለካከት የተለያየ ነው።”—ታማራ
“እኔና ሚስቴ በአስተዳደጋችን ምክንያት ገንዘብ ከማውጣት ጋር በተያያዘ የተለያየ አመለካከት አለን። ከተጋባን በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ስለ ገንዘብ እንጨቃጨቅ ነበር። ስምምነት ላይ መድረስ የቻልነው ብዙ ከተነጋገርን በኋላ ነው።”—ታይለር
አንዳንድ ችግሮች በመደራደር ብቻ የሚፈቱ አይደሉም። ለምሳሌ የአንዳቸው ወላጅ ቢታመምና እንክብካቤ ቢያስፈልገውስ? ወይም ደግሞ አንዳቸው ልጅ መውለድ ቢፈልጉስ? a
“ከባለቤቴ ጋር ልጅ መውለድን በተመለከተ በተደጋጋሚ ተነጋግረናል። እሷ ልጅ የመውለድ ፍላጎቷ እየጨመረ ነው፤ አመለካከታችን እየተራራቀ መጥቷል። መደራደር የምንችልበት መንገድ አይታየኝም።”—አሌክስ
አመለካከታችሁ ስለተለያየ ብቻ ትዳራችሁ ተስፋ የለውም ማለት አይደለም። አንዳንድ ባለሙያዎች ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ከባድ በሆነ ጉዳይ ላይ መስማማት ካቃታችሁ ትዳሩን ማፍረስ ቢኖርባችሁ እንኳ እንደምንም ብላችሁ መብታችሁን ማስከበር እንዳለባችሁ ይናገራሉ። ሆኖም ይህ ምክር፣ ምንም ይምጣ ምን እንደማትለያዩ በአምላክ ፊት የገባችሁትን ቃል ኪዳን ችላ በማለት በራሳችሁ ስሜት ላይ ብቻ እንድታተኩሩ ያደርጋችኋል።
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
የጋብቻ ቃለ መሐላችሁን ለማክበር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። እንዲህ ማድረጋችሁ አንዳችሁ ሌላውን ለማሸነፍ ከመሞከር ይልቅ ልዩነታችሁን ለመፍታት ተባብራችሁ እንድትሠሩ ያነሳሳችኋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”—ማቴዎስ 19:6
ወጪያችሁ አስሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳችሁ ልጅ መውለድ ትፈልጋላችሁ እንበል፤ አንዳችሁ ግን አትፈልጉም። በዚህ ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባት ያለባችሁ ብዙ ነገር አለ፤ ለምሳሌ፦
የትዳራችሁ ጥንካሬ
ልጅ መውለድ የሚያስከትለው ጫና በትዳራችሁ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
ወላጅ መሆን የሚያስከትለው ኃላፊነት
ልጅ ማሳደግ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ከማሟላት ያለፈ ነገር ይጠይቃል።
የገንዘብ አቅማችሁ
ሥራችሁን እንዲሁም የቤተሰብና ሌሎች ኃላፊነቶቻችሁን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት ትችላላችሁ?
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ . . . በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?”—ሉቃስ 14:28
ጉዳዩን ከተለያየ አቅጣጫ ለማየት ሞክሩ። እንዲህ ካደረጋችሁ አንዳንድ የአመለካከት ልዩነቶችን መፍታት ትችሉ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ያጋጫችሁ ልጅ የመውለድ ጉዳይ ከሆነ ልጅ የማይፈልገው የትዳር አጋር እነዚህን ጥያቄዎች ራሱን ሊጠይቅ ይችላል፦
‘ልጅ መውለድ አልፈልግም ስል ጨርሶ ልጅ አልፈልግም ማለቴ ነው ወይስ አሁን አልፈልግም?’
‘ልጅ የማልፈልገው ጥሩ ወላጅ መሆን እንደማልችል ስለሚሰማኝ ነው?’
‘ልጅ የማልፈልገው የትዳር ጓደኛዬ ችላ እንዳትለኝ ስለምፈራ ነው?’
በሌላ በኩል ደግሞ ልጅ የሚፈልገው የትዳር አጋር የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሱን ሊጠይቅ ይችላል፦
‘ወላጅ መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁ ነን?’
‘የገንዘብ አቅማችን ልጅ ለማሳደግ ይፈቅድልናል?’
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ‘ከሰማይ የሆነው ጥበብ ምክንያታዊ ነው።’—ያዕቆብ 3:17
የትዳር አጋራችሁ አመለካከት ያለውን መልካም ጎን አስቡ። ሁለት ሰዎች አንድ ዓይነት ነገር እየተመለከቱ ስለዚያ ነገር የተለያየ እይታ ሊኖራቸው ይችላል። በተመሳሳይም ባለትዳሮች ስለ አንድ ጉዳይ የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል፤ ለምሳሌ ገንዘባችንን በምን ላይ እናውለው ስለሚለው ጉዳይ ያላቸው አመለካከት ይለያይ ይሆናል። አመለካከታችሁ በሚለያይባቸው ጉዳዮች ላይ ስትወያዩ ከሚያስማሟችሁ ነጥቦች ጀምሩ።
የጋራ ፍላጎታችሁ ምንድን ነው?
እያንዳንዱ አመለካከት ምን መልካም ጎን አለው?
ለትዳራችሁ ስትሉ አንዳችሁ ወይም ሁለታችሁም አመለካከታችሁን መቀየር ትችሉ ይሆን?
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።”—1 ቆሮንቶስ 10:24