በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጆች ጽናትን እንዲያዳብሩ መርዳት

ልጆች ጽናትን እንዲያዳብሩ መርዳት

 ልጃችሁ “በቃ አቃተኝ!” እያለ ያለቅሳል። “በጣም ከባድ ነው! መቼም አልችለውም!” ይላችኋል። አንድን ነገር ማከናወን በጣም ስለከበደው ብዙ ሳይሞክር ተስፋ ወደ መቁረጥ እያመራ ነው። ልጃችሁ ሲቸገር ማየት ቢያሳዝናችሁም ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መወጣትን እንዲማር ደግሞ ትፈልጋላችሁ። ታዲያ ቶሎ ጣልቃ ገብታችሁ ብትረዱት ወይም “በቃ ተወው” ብትሉት ይሻላል? ወይስ በዚህ አጋጣሚ ልጃችሁ ጽናትን እንዲያዳብር ልትረዱት ትችላላችሁ?

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

 ጽናት ወሳኝ ባሕርይ ነው። ወላጆች ልጃቸው ተግቶ በመሥራት ክህሎቱን እንዲያዳብር የሚያስተምሩት ከሆነ በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት የማምጣት ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል፤ የተሻለ ስሜታዊና አካላዊ ጤንነት ይኖረዋል፤ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ጠንካራና ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ቀላል ይሆንለታል። በተቃራኒው ወላጆች ልጃቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዳያጋጥሙትና ስህተት እንዳይሠራ የሚከላከሉለት ከሆነ በጭንቀት የመዋጥ አጋጣሚው ሰፊ ይሆናል፤ ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት ያዳብራል፤ እንዲሁም አዋቂ ከሆነ በኋላ አርኪ ሕይወት የመምራት ዕድሉ አናሳ ይሆናል።

 ጽናት ሊዳብር ይችላል። ትናንሽ ልጆችም እንኳ ፈታኝ የሆኑ ሥራዎችን ዳር ለማድረስ እንዲሁም ችግሮችን ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያጠናከሩ መርዳት ይቻላል። በዚህ ዙሪያ በተደረገ አንድ ጥናት ላይ የ15 ወር ሕፃናት አንድ አዋቂ ያለምንም ጥረት አንድን ነገር ሲሠራ ከሚያዩ ይልቅ ታግሎ ሲሠራው ሲያዩ የሚከብዳቸውን ነገር ታግለው ለመሥራት ያላቸው ተነሳሽነት እንደሚጨምር ተመራማሪዎች አስተውለዋል።

 “ሴት ልጆቼ ትንሽ እያሉ ጫማቸውን ማሰር እንዴት እንዳስተማርኳቸው ትዝ ይለኛል። ይህ በአንድ ጀምበር ሊማሩ የሚችሉት ነገር አይደለም። ጫማቸውን ማሰር ባስፈለጋቸው ቁጥር ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ያህል ብቻቸውን ቁጭ ብለው እንዴት እንደሚታሰር ለማስታወስ ይታገላሉ። ከዚያ እረዳቸዋለሁ። ለተወሰኑ ወራት ያህል መታገል አስፈልጓቸዋል፤ እንዲያውም አንዳንዴ ያለቅሱ ነበር። በኋላ ግን ለመዱት። ማሰሪያ የሌለው ጫማ ብገዛላቸው ለእኔ ግልግል ነበር። አንዳንዴ ግን ልጆቻችንን ጽናት ለማስተማር እኛ ወላጆች ራሳችን መጽናት ይኖርብናል።”—ኮሊን

 ጽናት ሊዳከም ይችላል። አንዳንድ ወላጆች ሳይታወቃቸው የልጃቸውን ጽናት ሊያዳክሙ ይችላሉ። እንዴት? ልጃቸው ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመው እንዳያዝን ወይም ተስፋ እንዳይቆርጥ በመስጋት ቶሎ እሱን ወደ መርዳት ይሄዳሉ፤ እንዲህ ማድረጋቸው ልጃቸው ጥሩ ስሜት እንዲሰማው እንደሚያደርግ ያስባሉ። ሆኖም ይህ አካሄድ ያልተፈለገ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። ጄሲካ ሌሂ የተባሉ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል፦ “ልጆቻችንን ከአስቸጋሪ ሁኔታ ባዳንናቸው . . . ቁጥር አንድ ግልጽ መልእክት እያስተላለፍንላቸው ነው፤ ብቁ ናቸው ወይም ይችላሉ ብለን እንደማናምን እንዲሁም እምነት እንደማንጥልባቸው እየነገርናቸው ነው።” a ይህ ምን ውጤት አለው? ወደፊት አንድ ተፈታታኝ ነገር ሲያጋጥማቸው የሆነ አዋቂ ጣልቃ ገብቶ ሊያድናቸው እንደሚገባ ስለሚሰማቸው ቶሎ ተስፋ ወደ መቁረጥ ሊሄዱ ይችላሉ።

ልጃችሁ አንድን ነገር ማድረግ ሲከብደው ጣልቃ ገብታችሁ ከመርዳት ይልቅ አጋጣሚውን ጽናትን ለማስተማር ተጠቀሙበት

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

 ተግተው እንዲሠሩ አበረታቷቸው። ወላጆች ለልጆቻቸው ዕድሜያቸውን የሚመጥን ሥራ በመስጠት ጽናትን እንዲያዳብሩ ሊረዷቸው ይችላሉ። ለምሳሌ ገና ትምህርት ቤት ያልገቡ ልጆች ልብሳቸውን በሥርዓት እንዲያስቀምጡና መጫወቻቸውን እንዲሰበስቡ ማድረግ ይቻላል። ትንሽ ከፍ ያሉ ልጆች አስቤዛዎችን ቦታ ቦታ አስይዘው እንዲያስቀምጡ፣ ሳህን እንዲያቀራርቡና የተበላበትን እንዲያነሳሱ፣ ቆሻሻ አውጥተው እንዲጥሉ እንዲሁም ወለል ላይ የወዳደቁ ነገሮችን እንዲያጸዱ ልታደርጉ ትችላላችሁ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ደግሞ ከጽዳትና ከጥገና ጋር የተያያዙ ከበድ ያሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ ማድረግ ይቻላል። ልጆች ሥራ መሥራት ላይፈልጉ ይችላሉ፤ ሆኖም ወላጆች ከትንሽነታቸው አንስቶ በቤት ውስጥ ከሚከናወነው ሥራ ጋር በተያያዘ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ኃላፊነት የሚሰጧቸው ከሆነ ልጆቹ ይጠቀማሉ። እንዴት? አዋቂ ከሆኑ በኋላ፣ ፈታኝ የሆኑ ሆኖም የግድ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ሲያጋጥሟቸው ከመሸሽ ይልቅ ራስን አስገድዶ መሥራትን ይማራሉ።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል።”​—ምሳሌ 14:23

 “ልጆቻችሁ አርፈው እንዲቀመጡ ብቻ የሚያደርግ ሥራ በመስጠት ጊዜው እንዲባክን አታድርጉ። ልጆችን ጨምሮ ማንም ሰው በዚህ አይደሰትም። በሆነ ነገር እንዳገዙ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ሥራ ስጧቸው። ልጃችሁ ትንሽ ከሆነ ቁመቱ በሚደርስባቸው አካባቢዎች አቧራ እንዲጠራርግ ልትነግሩት ትችላላችሁ። መኪና እያጠባችሁ ከሆነ ለእናንተ ለመድረስ አመቺ ያልሆኑትን ከታች ከታች ያሉትን ቦታዎች እንዲያጸዳ አድርጉ። ጠንክሮ በመሥራቱ ማመስገናችሁንም አትርሱ።”—ክሪስ

 ከበድ ያሉ ሥራዎችን ሲሠሩ ጥሩ አድርጋችሁ ምሯቸው። አንዳንድ ጊዜ ልጆች አንድን ሥራ እንዴት ማከናወን እንዳለባቸው ስለማያውቁ በቀላሉ ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። ስለዚህ ልጃችሁን አንድ አዲስ ነገር ስታስተምሩት የሚከተለውን ዘዴ ልትሞክሩ ትችላላችሁ። በመጀመሪያ፣ ሥራውን እናንተ ስትሠሩ እንዲያያችሁ አድርጉ። ከዚያ አብራችሁ ሥሩ። ቀጥሎ ደግሞ እሱ ሲሠራ እያያችሁት ጠቃሚ ሐሳቦችን አካፍሉት። በመጨረሻም ሙሉ በሙሉ ራሱን ችሎ እንዲሠራ አድርጉ።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ።”​—ዮሐንስ 13:15

 “ከራሴ ተሞክሮ እንዳየሁት ልጆቻችን ጽናትን እንዲያዳብሩ ከፈለግን እኛ ወላጆች ምሳሌ ሆነን መገኘት አለብን። እነሱ እንዲያዳብሩ የምንፈልገውን ባሕርይ እኛ ራሳችን ማሳየት ይኖርብናል።”—ዳግ

 ምንም ነገር ለማድረግ የማይቸገርና ስህተት የማይሠራ ሰው እንደሌለ አምነው እንዲቀበሉ እርዷቸው። አንድን ነገር ለማድረግ ተቸግራችሁ ስለነበረበት ጊዜና በወቅቱ ተስፋ ባለመቁረጣችሁ ስላገኛችሁት ጥቅም ለልጃችሁ ንገሩት። አንድን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ስናደርገው መቸገራችን የሚጠበቅ ነገር እንደሆነ፣ ብሎም ስህተት መሥራት ለመማር የሚያስችል አጋጣሚ እንደሚሰጥ ግለጹለት። ስህተት መሥራቱ ለእሱ ያላችሁን ፍቅር እንደማይቀንሰው አረጋግጡለት። ጡንቻ የሚዳብረው ስናሠራው እንደሆነ ሁሉ የልጃችሁ ጽናትም የሚዳብረው ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዲጋፈጥ ስትፈቅዱለት ነው። ስለዚህ ልጃችሁ አንድን ነገር ለማድረግ ሲቸገር ቶሎ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ ሁኔታው ቢያበሳጨውም በራሱ ለመወጣት የሚሞክርበት ጊዜ ስጡት። ሀው ችልድረን ሰክሲድ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ታዳጊ ጠንካራና በሳል እንዲሆን መርዳት የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ስህተት ሊሠራ የሚችልበት ሰፊ አጋጣሚ እንዳለ እያወቅንም ያን ነገር እንዲሞክረው መፍቀድ ነው።”

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰው በልጅነቱ ቀንበር ቢሸከም ጥሩ ነው።”​—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:27

 “ልጆች አስፈላጊ ሲሆን የእኛ እርዳታ እንደማይለያቸው እንዲያውቁ እስካደረግን ድረስ አንዳንድ ከባድ ሁኔታዎችን በራሳቸው እንዲጋፈጡ ብንተዋቸው ይጠቀማሉ። ከብዷቸው የነበረው ነገር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደ ቀድሞው አያታግላቸውም፤ በመጽናታቸው ችሎታ ብቻ ሳይሆን በራስ የመተማመን ስሜትም ያዳብራሉ።”—ጆርዳን

 ለችሎታቸው ሳይሆን ለጥረታቸው አመስግኗቸው። ለምሳሌ ልጃችሁን “በጣም ጥሩ ውጤት ነው ያመጣኸው! የሚገርም ጭንቅላት አለህ” ከማለት ይልቅ “በጣም ጥሩ ውጤት ነው ያመጣኸው! ምን ያህል ጠንክረህ እንዳጠናህ ያሳያል” ልትሉት ትችላላችሁ። ልጆችን ከችሎታቸው ይልቅ ለጥረታቸው ማመስገናችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ለችሎታቸው የምናመሰግናቸው ከሆነ “አንድ ነገር ከከበዳቸው ወይም የሆነ ስህተት ከሠሩ ወዲያውኑ ራሳቸውን መጠራጠር ይጀምራሉ” በማለት ዶክተር ካረል ድዌክ ተናገረዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ወላጆች ለልጆቻቸው ሊሰጡ የሚችሉት ከሁሉ የተሻለው ስጦታ ልጆቻቸው ፈታኝ ሁኔታዎችን የሚወዱ፣ ስህተት መሥራት ይበልጥ ለመመራመር የሚያነሳሳቸው፣ ጥረት ማድረግ የሚያስደስታቸው፣ አዳዲስ የአሠራር ዘዴዎችን የሚቀይሱና የመማር ጉጉት ያላቸው እንዲሆኑ አድርጎ ማሳደግ ነው። እንዲህ ዓይነት አስተዳደግ ያላቸው ልጆች፣ ሁሌ ካልተመሰገንኩ የሚል አመለካከት አያድርባቸውም።” b

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “[ሰው] በሚቀበለው ውዳሴ ይፈተናል።”​—ምሳሌ 27:21

a ዘ ጊፍት ኦቭ ፌይሊየር ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።

b ማይንድሴት ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።