በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ፍቺ በልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

ፍቺ በልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

 ተስማምተው መኖር ያቃታቸው አንዳንድ ባለትዳሮች፣ ልጆቻቸው የእነሱን ንትርክ እያዩ ከሚያድጉ ቢፋቱ የተሻለ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እውነታው ግን ይህ ነው?

 ፍቺ በልጆች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

 ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፍቺ በልጆች ላይ ከባድ ጉዳት ያስከትላል። ወላጆቻቸው የተፋቱባቸው ልጆች . . .

  •   ቁጡ ሊሆኑ፣ በጭንቀት ሊዋጡና የመንፈስ ጭንቀት ሊይዛቸው ይችላል

  •   ባሕርያቸው ሊበላሽ ይችላል

  •   በትምህርታቸው ወደኋላ ሊቀሩ ወይም ሊያቋርጡ ይችላሉ

  •   በቀላሉ በበሽታ ሊጠቁ ይችላሉ

 ከዚህም ሌላ ብዙ ልጆች፣ ወላጆቻቸው በመፋታታቸው ጥፋተኝነት ይሰማቸዋል፤ ወላጆቻቸው የተፋቱት በእነሱ ምክንያት እንደሆነ ወይም ፍቺውን ማስቀረት ይችሉ እንደነበር ያስባሉ።

 ፍቺ፣ ልጆቹ ካደጉ በኋላም ተጽዕኖ ሊያደርግባቸው ይችላል፤ ወላጆቻቸው የተፋቱባቸው ልጆች በራሳቸው መተማመን እንዲሁም ሌሎችን ማመን ሊከብዳቸው ይችላል። በተጨማሪም እንዲህ ያሉት ልጆች ትዳር ከመሠረቱ በኋላ ችግር ሲያጋጥማቸው የመፋታታቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው።

 ዋናው ነጥብ፦ ለመፋታት የሚያስቡ አንዳንድ ሰዎች፣ ፍቺ ለልጆቻቸው የተሻለ እንደሆነ ቢሰማቸውም ጥናቶች ይህን አይደግፉም። የልጆች ደህንነት ባለሙያ የሆኑት ፔነሎፒ ሊክ “ፍቺ የልጆቹን ሕይወት ያተራምሰዋል” በማለት ጽፈዋል። a

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:4

 ብንፋታ ልጃችን ደስተኛ ይሆናል?

 አንዳንድ ሰዎች እንደዚያ ይሰማቸዋል። ይሁንና ወላጅ የሚፈልገውና ልጁ የሚፈልገው ነገር የተለያየ ሊሆን እንደሚችል እናስታውስ። ለመፋታት የሚያስበው ወላጅ፣ አዲስ ሕይወት መጀመር ይፈልጋል። ልጅየው ግን በአብዛኛው ሕይወቱ ባይቀየርና ከአባቱና ከእናቱ ጋር አብሮ ቢኖር ይመርጣል።

 ዚ አንኤክስፔክትድ ሌጋሲ ኦቭ ዲቮርስ የተባለው መጽሐፍ ጸሐፊዎች፣ በሺዎች በሚቆጠሩ የተፋቱ ባለትዳሮች ሕይወት ላይ ጥናት ካደረጉ በኋላ እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ነገር ግልጽ ነው፦ ልጆቹ ወላጆቻቸው በመፋታታቸው ደስተኛ እንደሆኑ አይገልጹም። እንዲያውም ‘ልጅነቴን ያጣሁት ወላጆቼ ሲፋቱ ነው’ ብለው በግልጽ ይናገራሉ።” መጽሐፉ አክሎ እንደገለጸው ልጆቹ፣ በቅርብ የሚያውቁት ዝምድና መፍረሱ በቀረው ዓለም ላይ እምነት መጣል እንዲከብዳቸውና ስጋት እንዲያድርባቸው ያደርጋል።

 ዋናው ነጥብ፦ ልጆች፣ ወላጆቻቸው ከተፋቱ በኋላ ብዙውን ጊዜ ደስተኛ አይሆኑም።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የተደቆሰ መንፈስ . . . ኃይል ያሟጥጣል።”—ምሳሌ 17:22

 ተለያይቶ ልጅ ማሳደግን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

 አንዳንድ የተፋቱ ሰዎች ልጅ የማሳደግ ኃላፊነታቸውን እኩል በመጋራት፣ አብረው ቢኖሩ ኖሮ በሚያደርጉት መንገድ ልጃቸውን ለማሳደግ ይጥራሉ። ሆኖም የተፋቱ ወላጆች ለየብቻ ሆነው ልጃቸውን ማሳደግ ቀላል አይሆንላቸውም። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የተፋቱ ወላጆች በአብዛኛው . . .

  •   ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ይቀንሳል

  •   ለልጆቻቸው የሚያስተምሩት ነገር እርስ በርሱ የሚጋጭ ይሆናል

  •   የጥፋተኝነት ስሜት ስለሚሰማቸው ወይም ስለሚደክማቸው ልጆቻቸውን ያቀብጧቸዋል

 በተጨማሪም ወላጆቹ የተፋቱበት ልጅ፣ በወላጆቹ ሥልጣን ላይ ሊያምፅ ይችላል። ደግሞም ወላጆቹ ትክክለኛውን ነገር በማድረግ ምሳሌ አልሆኑትም፤ ለምሳሌ የገቡትን ቃል ወይም ስምምነታቸውን አላከበሩም። በመሆኑም ልጁ ‘እነሱን የምሰማው ለምንድን ነው?’ ብሎ ሊያስብ ይችላል።

 ዋናው ነጥብ፦ የተፋቱ ወላጆች ለየብቻ ሆነው ልጃቸውን ማሳደግ ብዙውን ጊዜ ቀላል አይሆንላቸውም። ለልጆቹ ደግሞ ሁኔታው የባሰ ከባድ ይሆንባቸዋል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ተስፋ እንዳይቆርጡ ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው።”—ቆላስይስ 3:21 የግርጌ ማስታወሻ

 የተሻለ አማራጭ ይኖር ይሆን?

 የተፋቱ ሰዎች አዲስ ሕይወት ለመጀመር የሚያደርጉትን ጥረት፣ ቀድሞውንም ትዳራቸውን ለመታደግ ቢያውሉት ብዙውን ጊዜ የተሻለ ይሆን ነበር። ዘ ኬዝ ፎር ሜሬጅ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “አንዳንድ ጊዜ እንደምናስበው አንድ ትዳር ችግር ስላለበት ብቻ ሁልጊዜ በዚያ ሁኔታ ይቀጥላል ማለት አይደለም። . . . ደስተኛ ባይሆኑም አብረው መኖራቸውን የቀጠሉ ብዙ ባለትዳሮች ከጊዜ በኋላ ደስተኛ ትዳር ሊኖራቸው ችሏል።” በጥቅሉ ሲታይ፣ ለልጆች የተሻለ የሚሆነው ወላጆች አብረው መኖራቸው ነው።

 ይህ ሲባል ግን ፍቺ ፈጽሞ ሊታሰብ የማይገባው ነገር ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ አንደኛው ወገን የፆታ ብልግና ከፈጸመ መፋታት እንደሚቻል ይገልጻል። (ማቴዎስ 19:9) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ . . . አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” በማለትም ይናገራል። (ምሳሌ 14:15) በመሆኑም በትዳራቸው ውስጥ ችግር የገጠማቸው ባልና ሚስት፣ ፍቺ በልጆቻቸው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ጨምሮ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል።

 እርግጥ ነው፣ ሳይፋቱ አብሮ መኖር ብቻውን በቂ አይደለም። ባለትዳሮች፣ ዘላቂና አስደሳች ለሆነ ትዳር አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያትን ለማፍራት የሚረዷቸውን ከሁሉ የተሻሉ ምክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማግኘት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉ ምክሮችን መያዙ አያስገርምም፤ ምክንያቱም የጋብቻ ዝግጅትን ያቋቋመው የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነው ይሖዋ ነው።—ማቴዎስ 19:4-6

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ . . . እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።”—ኢሳይያስ 48:17

a ዩር ግሮዊንግ ቻይልድ—ፍሮም ቤቢሁድ ስሩ አዶለሰንስ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።