የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
መዝሙር 23:4—“በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ”
“ድቅድቅ ጨለማ በዋጠው ሸለቆ ውስጥ ብሄድ እንኳ አንተ ከእኔ ጋር ስለሆንክ፣ ጉዳት ይደርስብኛል ብዬ አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ ያበረታቱኛል።”—መዝሙር 23:4 አዲስ ዓለም ትርጉም
“በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል።”—መዝሙር 23:4 የ1954 ትርጉም
የመዝሙር 23:4 ትርጉም a
አምላክ ለአገልጋዮቹ ምንጊዜም ጥበቃ ያደርግላቸዋል፤ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ ጥበቃው አይለያቸውም። ጥቅሱ አምላክ ለአገልጋዮቹ ጥበቃ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ለማሳየት በእረኛቸው ጥበቃ ሥር ያሉ በጎችን እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀማል። b የአምላክ አገልጋዮች ድቅድቅ ጨለማ የዋጠው ሸለቆ ውስጥ እንደ መግባት ወይም ሞትን እንደ መጋፈጥ ያሉ አስጨናቂ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ብቻቸውን እንደሆኑ አይሰማቸውም። አምላክ ቃል በቃል ከአጠገባቸው እንዳለ ያህል ሆኖ ስለሚሰማቸው ስጋት አያድርባቸውም።
መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን አንድ እረኛ በጎቹን ከአውሬ ለመጠበቅ በትር ወይም ዱላ ይጠቀም ነበር። በተጨማሪም በጎቹን ለመምራት ወይም አደጋ ሊፈጥር ከሚችል ሁኔታ ጎትቶ ለመመለስ ምርኩዙን ይጠቀማል፤ ይህ ምርኩዝ በአብዛኛው በአንደኛው ጫፍ ላይ ቆልመም ያለ ረጅም ዱላ ነው። ይሖዋ አምላክም ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ እረኛ አገልጋዮቹን ይጠብቃል እንዲሁም ይመራል። እንደ ድቅድቅ ጨለማ ያለ ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ጊዜም እንኳ በተለያዩ መንገዶች እንክብካቤ ያደርግላቸዋል።
በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት መመሪያና ማጽናኛ ይሰጣቸዋል።—ሮም 15:4
ጸሎታቸውን በመስማት ውስጣዊ ሰላም ይሰጣቸዋል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ሌሎች አገልጋዮቹን ተጠቅሞ ያበረታታቸዋል።—ዕብራውያን 10:24, 25
ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ አስተማማኝ ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤ አሁን እየደረሰባቸው ያለውን ማንኛውንም ችግር እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል።—መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3-5
የመዝሙር 23:4 አውድ
መዝሙር 23ን የጻፈው በልጅነቱ እረኛ የነበረውና ከጊዜ በኋላ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የሆነው ዳዊት ነው። (1 ሳሙኤል 17:34, 35፤ 2 ሳሙኤል 7:8) ይህ መዝሙር የሚጀምረው ልክ አንድ እረኛ ለበጎቹ እንደሚያደርገው ይሖዋም አገልጋዮቹን እንደሚመራቸው፣ እንደሚመግባቸውና ኃይላቸውን እንደሚያድስላቸው በመግለጽ ነው።—መዝሙር 23:1-3
ከቁጥር 1 እስከ 3 ድረስ፣ ዳዊት ስለ ይሖዋ ሲናገር “እሱ” የሚለውን አገላለጽ ተጠቅሟል፤ ቁጥር 4 ላይ ግን አምላክ ስለሚያደርግለት ጥበቃ ሲናገር የተጠቀመው “አንተ” የሚለውን አገላለጽ ነው። ይህ ቀላል የሚመስል ለውጥ ዳዊት ከይሖዋ ጋር ምን ያህል የጠበቀ ዝምድና እንዳለው ያሳያል። ዳዊት አምላክ እንደሚያስብለትና በሕይወቱ ውስጥ ስለሚያጋጥሙት ፈተናዎች እንደሚያውቅ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ የሚፈራበት ምንም ምክንያት አልነበረም።
መዝሙር 23 መጀመሪያ ላይ አንድን እረኛና በጎቹን እንደ ምሳሌ አድርጎ ሲጠቀም ከቆየ በኋላ ቁጥር 5 እና 6 ላይ አንድን ጋባዥና እንግዳውን እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀማል። አንድ ደግ ጋባዥ እንግዶቹን በክብር እንደሚይዝ ሁሉ ይሖዋም ዳዊትን በክብር ይይዘዋል። የዳዊት ጠላቶችም እንኳ አምላክ ለዳዊት እንክብካቤ እንዳያደርግለት መከላከል አይችሉም። ዳዊት በመዝሙሩ መጨረሻ ላይ አምላክ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ጥሩነትና ፍቅር እንደሚያሳየው ያለውን እምነት ገልጿል።
በመዝሙር 23 ላይ የሚገኙት ምሳሌዎች አምላክ ለአገልጋዮቹ የሚያደርገውን ቀጣይ የሆነ ፍቅራዊ እንክብካቤ ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ።—1 ጴጥሮስ 2:25
a ይህ መዝሙር በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ የሚገኘው መዝሙር 22 ላይ ነው። በአጠቃላይ 150 መዝሙሮች ቢኖሩም አንዳንድ ትርጉሞች የመዝሙሮቹን ቁጥር የመደቡት በዕብራይስጡ የማሶሬቶች ጽሑፍ መሠረት ሲሆን ሌሎች ትርጉሞች ደግሞ የግሪክኛውን ሰብዓ ሊቃናት አቆጣጠር ተከትለዋል፤ ሰብዓ ሊቃናት በሁለተኛው ዓ.ዓ. የተጠናቀቀ የዕብራይስጡ ጽሑፍ ትርጉም ነው።
b ስሙ ይሖዋ የሆነው አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ አፍቃሪ ከሆነ እረኛ ጋር ተመሳስሏል። በበጎች የተመሰሉት አገልጋዮቹ ጥበቃና ድጋፍ ለማግኘት በእሱ ይታመናሉ።—መዝሙር 100:3፤ ኢሳይያስ 40:10, 11፤ ኤርምያስ 31:10፤ ሕዝቅኤል 34:11-16