የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
መዝሙር 37:4—“በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ”
“በይሖዋ ሐሴት አድርግ፤ እሱም የልብህን መሻት ይሰጥሃል።”—መዝሙር 37:4 አዲስ ዓለም ትርጉም
“በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።”—መዝሙር 37:4 አዲሱ መደበኛ ትርጉም
የመዝሙር 37:4 ትርጉም
መዝሙራዊው፣ የአምላክ አገልጋዮች ከአምላክ ጋር ባላቸው የቀረበ ወዳጅነት ደስ እንዲላቸው አበረታቷል። እንዲህ ያለ ወዳጅነት ያላቸው ሁሉ፣ ይሖዋ a አምላክ ተገቢ የሆኑ ምኞቶቻቸውን እንደሚፈጽምላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።
“በይሖዋ ሐሴት አድርግ።” ይህ አገላለጽ “በይሖዋ በጣም ደስ ይበልህ፣” “ጌታን በማገልገል ተደሰት” ወይም “ጌታ በገባልህ ቃል ተደሰት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። በአጭር አነጋገር እውነተኛውን አምላክ በማምለካችን “እጅግ ደስ [ሊለን]” ይገባል። (መዝሙር 37:4 የግርጌ ማስታወሻ) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች የእሱ ዓይነት አመለካከት አላቸው፤ የአምላክ አመለካከት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል። አምላክን በማወቅ ብቻ አይወሰኑም፤ እሱን መታዘዝ ጥበብ እንደሆነም ከልባቸው ያምናሉ። ይህም ንጹሕ ሕሊና እንዲኖራቸውና ከብዙ መዘዞች እንዲጠበቁ ይረዳቸዋል። (ምሳሌ 3:5, 6) ለምሳሌ፣ ስግብግብ ወይም አጭበርባሪ የሆኑ ሰዎች የተሳካላቸው መስለው ቢታዩ፣ የአምላክ አገልጋዮች አይበሳጩም ወይም አይቀኑም። (መዝሙር 37:1, 7-9) አምላክ በቅርቡ ግፍን እንደሚያስወግድና ጥሩ ምግባር ያላቸው ታማኝ ሰዎችን እንደሚባርክ ያውቃሉ፤ ይህም ደስተኞች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። (መዝሙር 37:34) የሰማዩ አባታቸውን ሞገስ እንዳገኙ ማወቃቸውም በጣም ያስደስታቸዋል።—መዝሙር 5:12፤ ምሳሌ 27:11
“የልብህን መሻት ይሰጥሃል።” ይህ ሐሳብ “ጸሎትህን ይሰማሃል” ወይም “በጣም የምትመኘውን ነገር ይሰጥሃል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። በእርግጥ ይህ ሲባል፣ ይሖዋ የጠየቅነውን ሁሉ ይሰጠናል ማለት አይደለም። እንደ አንድ ጥሩ ወላጅ ሁሉ ይሖዋም ለልጆቹ የሚበጀውን ያውቃል። በተጨማሪም የምንለምነው ነገርና አኗኗራችን ከእሱ መሥፈርቶችና ከፈቃዱ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። (ምሳሌ 28:9፤ ያዕቆብ 4:3፤ 1 ዮሐንስ 5:14) ይህን የምናሟላ ከሆነ “ጸሎት ሰሚ” የሆነው አምላክ ልመናችንን እንደሚሰማ በመተማመን ወደ እሱ መጸለይ እንችላለን።—መዝሙር 65:2፤ ማቴዎስ 21:22
የመዝሙር 37:4 አውድ
መዝሙር 37ን ያቀናበረው በጥንቷ እስራኤል የኖረው ንጉሥ ዳዊት ነው። መዝሙሩን የጻፈው በፊደል ቅደም ተከተል ነው። b
ዳዊት ብዙ ግፍ ተፈጽሞበታል። ንጉሥ ሳኦል እያደነው ነበር፤ ዳዊትን ሊገድሉት የሚፈልጉ ሌሎችም ነበሩ። (2 ሳሙኤል 22:1) ያም ሆኖ ዳዊት በአምላኩ ሙሉ በሙሉ ይተማመን ነበር። ይዋል ይደር እንጂ ይሖዋ ለክፉዎች የእጃቸውን እንደሚሰጣቸው ዳዊት ያውቅ ነበር። (መዝሙር 37:10, 11) “እንደለመለመ ተክል” ያማረባቸው ቢመስሉም መክሰማቸው አይቀርም።—መዝሙር 37:2, 20, 35, 36
መዝሙር 37 የአምላክን መመሪያዎች የሚታዘዙና የማይታዘዙ ሰዎች መጨረሻቸው ምን እንደሚሆን እያነጻጸረ ያስቀምጣል። (መዝሙር 37:16, 17, 21, 22, 27, 28) በመሆኑም ይህ መዝሙር ጥበበኞችና አምላክ የሚደሰትብን ዓይነት ሰዎች ለመሆን ይረዳናል።
የመዝሙር መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።
a ይሖዋ፣ በዕብራይስጥ የተቀመጠው የአምላክ ስም የተለመደ የአማርኛ አጠራር ነው። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በአምላክ የግል ስም ከመጠቀም ይልቅ “ጌታ” የሚለውን የማዕረግ ስም የመረጡት ለምን እንደሆነ ለማወቅ “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b በዚህ የአጻጻፍ ዘዴ፣ የመጀመሪያው ቁጥር ወይም የተወሰኑ ቁጥሮች የሚጀምሩት በመጀመሪያው የዕብራይስጥ ፊደል ነው፤ ቀጥሎ ያሉት የተወሰኑ ቁጥሮች ደግሞ በሁለተኛው ፊደል ይጀምራሉ፤ እንዲህ እያለ ይቀጥላል። በዚህ መንገድ የተቀመጠው መዝሙሩን ለማስታወስ እንዲረዳ ታስቦ ሊሆን ይችላል።