በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

መዝሙር 46:10—“ዕረፉ፣ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ”

መዝሙር 46:10—“ዕረፉ፣ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ”

 “አርፋችሁ ተቀመጡ፤ እኔ አምላክ እንደሆንኩም እወቁ። በብሔራት መካከል ከፍ ከፍ እላለሁ፤ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።”—መዝሙር 46:10 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ዕረፉ፤ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ ዕወቁ፤ በሕዝቦች ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፤ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።”—መዝሙር 46:10 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የመዝሙር 46:10 ትርጉም

 አምላክ ሰዎች ሁሉ እሱን እንዲያመልኩትና ምድርን የመግዛት መብት ያለው እሱ መሆኑን አምነው እንዲቀበሉ እያሳሰበ ነው። ታላቅ ኃይሉና የሁሉ የበላይ መሆኑ የማይካድ ነው፤ ለዘላለም መኖር የሚፈልግ ሁሉ ይህን ሐቅ መቀበል ይኖርበታል።—ራእይ 4:11

 “አርፋችሁ ተቀመጡ፤ እኔ አምላክ እንደሆንኩም እወቁ።” በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ፣ የዚህ ዓረፍተ ነገር የመጀመሪያ ክፍል “ጸጥ ብላችሁ” ተብሎ ተተርጉሟል። ይህ አተረጓጎም ሰዎች ስለ ጥቅሱ የተሳሳተ አመለካከት እንዲያድርባቸው አድርጓል፤ ጥቅሱ፣ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሆኑ በጥሞና መንፈስ እንዲቀመጡ ወይም ጸጥ እንዲሉ የሚያዝዝ ነው ብለው ያስባሉ። ሆኖም “አርፋችሁ ተቀመጡ፤ እኔ አምላክ እንደሆንኩም እወቁ” የሚለውን ዓረፍተ ነገር በዕብራይስጥ ብንመለከተው ይሖዋ a አምላክ ራሱ በሁሉም ብሔራት ለሚገኙ ሰዎች የሰጠው ማሳሰቢያ እንደሆነ እንረዳለን፤ እነዚህን ብሔራት፣ እሱን መቃወማቸውን እንዲያቆሙና አምልኮ የሚገባው እሱ ብቻ መሆኑን አምነው እንዲቀበሉ እያሳሰባቸው ነው።

 መዝሙር 2 ላይም ተመሳሳይ ማሳሰቢያ ይገኛል። በዚህ መዝሙር ላይም አምላክ እሱን በሚቃወሙት ሰዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ቃል ገብቷል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የአምላክን ሥልጣን የሚቀበሉ ሰዎች እሱ እንዲመራቸው እንዲሁም ብርታትና ጥበብ እንዲሰጣቸው ይጠይቁታል። እነዚህ ሰዎች ‘እሱን መጠጊያ ስለሚያደርጉ’ በአስቸጋሪ ጊዜም እንኳ በደስታና ያለስጋት ይኖራሉ።—መዝሙር 2:9-12

 “በብሔራት መካከል ከፍ ከፍ እላለሁ፤ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።” በጥንት ዘመን ይሖዋ አምላክ ታላቅ ኃይሉን ተጠቅሞ ሕዝቦቹን በታደጋቸው ጊዜ ከፍ ከፍ ብሎ ነበር። (ዘፀአት 15:1-3) ወደፊት ደግሞ ከዚህም በላቀ ደረጃ ከፍ ከፍ ይላል፤ ምክንያቱም ያን ጊዜ ምድር ላይ የሚኖር ሰው ሁሉ ለእሱ ሥልጣን ይገዛል እንዲሁም እሱን ብቻ ያመልካል።—መዝሙር 86:9, 10፤ ኢሳይያስ 2:11

የመዝሙር 46:10 አውድ

 አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ መዝሙር 46⁠ን “አምላክን ለኃይሉ፣ እንዲሁም የሕዝቡ ጠባቂ በመሆኑ የሚያወድስ መዝሙር” ሲል ገልጾታል። ጥንት የአምላክ ሕዝቦች መዝሙር 46⁠ን በመዘመር በይሖዋ የመጠበቅና የማዳን ችሎታ ላይ ያላቸውን እምነት ይገልጹ ነበር። (መዝሙር 46:1, 2) የመዝሙሩ ግጥም፣ ይሖዋ ምንጊዜም ከእነሱ ጋር እንደሆነ ያስታውሳቸው ነበር።—መዝሙር 46:7, 11

 መዝሙሩ፣ የይሖዋን አስደናቂ ሥራዎች መለስ ብለው እንዲያስቡ ጋብዟቸዋል፤ እንዲህ ማድረጋቸው በእሱ የማዳን ኃይል ላይ ያላቸው እምነት እንዲጠናከር ያደርጋል። (መዝሙር 46:8) ቀጥሎ ደግሞ፣ አምላክ ጦርነትን የማስቀረት ችሎታ እንዳለው ይገልጻል። (መዝሙር 46:9) በጥንት ዘመን፣ አምላክ ሕዝቦቹን ከጠላት ብሔራት የታደገባቸው ጊዜያት አሉ፤ በእነዚህ ጊዜያት ይሖዋ ጦርነትን አስቀርቷል ሊባል ይችላል። ሆኖም አምላክ በቅርቡ ከዚህ እጅግ የላቀ ነገር እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጣል፤ አምላክ ከመላው ምድር ላይ ጦርነትን ያስወግዳል።—ኢሳይያስ 2:4

 ይሖዋ ዛሬም እሱን የሚያመልኩትን ሰዎች ይጠብቃል? አዎ። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች በጻፈው ሐሳብ ላይ ‘እሱ ይረዳናል’ ብለው እንዲተማመኑ አበረታቷቸዋል። (ዕብራውያን 13:6) በመዝሙር 46 ላይ የሚገኘው ሐሳብ፣ በአምላክ የመታደግ ኃይል እንድንተማመን ይረዳናል። አምላክን “መጠጊያችንና ብርታታችን” አድርገን እንድናየው ያስችለናል።—መዝሙር 46:1

 የመዝሙር መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።