የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ማቴዎስ 6:34—‘ስለ ነገ አትጨነቁ’
የማቴዎስ 6:34 ትርጉም
በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የተናገረው ኢየሱስ ሲሆን አድማጮቹን ወደፊት ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ችግሮች በማሰብ ከልክ በላይ መጨነቅ እንደሌለባቸው መክሯቸዋል። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱን ቀን እንዳመጣጡ ማስተናገዳቸው የተሻለ ነው።
ኢየሱስ ስለ ነገ ማሰብ ወይም ለወደፊቱ ጊዜ ዕቅድ ማውጣት እንደሌለብን መናገሩ አልነበረም። (ምሳሌ 21:5) ከዚህ ይልቅ ገና ለገና ነገ ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት ከመጠን በላይ መጨነቅ እንደሌለብን ማስተማሩ ነበር። እንዲህ ያለው ጭንቀት ደስታ ሊያሳጣንና ማከናወን ያለብንን ነገር እንዳናከናውን እንቅፋት ሊፈጥርብን ይችላል። ዛሬ ላይ ሆነን በመጨነቅ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ችግሮች መፍታት አንችልም። ደግሞም የተጨነቅንበት ነገር አብዛኛውን ጊዜ ጨርሶ ላይከሰት ወይም የፈራነውን ያህል ከባድ ላይሆን ይችላል።
የማቴዎስ 6:34 አውድ
ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ፣ በብዙዎች ዘንድ በስፋት የሚታወቀውና በማቴዎስ ምዕራፍ 5-7 ላይ የሚገኘው የተራራው ስብከት ክፍል ነው። በተራራው ስብከቱ ላይ ኢየሱስ ከልክ ያለፈ ጭንቀት ሕይወታችንን ሊያሻሽልልንም ሆነ ዕድሜያችንን ሊያስረዝምልን እንደማይችል ገልጿል። (ማቴዎስ 6:27) በተጨማሪም በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ስለ ነገ ከልክ በላይ መጨነቅ እንደማያስፈልገን ተናግሯል። ተክሎችንና እንስሳትን የሚንከባከበው አምላክ እሱን የሚያገለግሉትን ሰዎችም ይንከባከባል።—ማቴዎስ 6:25, 26, 28-33
ማቴዎስ ምዕራፍ 6ን አንብብ፤ እንዲሁም ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የግርጌ ማስታወሻዎቹንና ማጣቀሻዎቹን ተመልከት።