የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ምሳሌ 22:6—“ልጅን ሊሄድበት በሚገባው መንገድ አሠልጥነው”
የምሳሌ 22:6 ትርጉም
ወላጆች፣ ልጆቻቸው አምላክን እንዲወዱና ሕጎቹን እንዲያከብሩ የሚያስተምሯቸው ከሆነ ይህ ሥልጠና በወደፊት ሕይወታቸው ላይ አዎንታዊና ዘላቂ ጥቅም እንደሚኖረው መተማመን ይችላሉ።
“ልጅን ሊሄድበት በሚገባው መንገድ አሠልጥነው።” ይህ ሐሳብ “ልጅህን ትክክለኛውን መንገድ አስጀምረው” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ወላጆች ልጆቻቸውን ትክክል እና ስህተት ስለሆነው ነገር ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዲያስተምሯቸው የምሳሌ መጽሐፍ ደጋግሞ ይመክራል። (ምሳሌ 19:18፤ 22:15፤ 29:15) ያም ሆኖ ወላጆች፣ እንደ አዋቂዎች ሁሉ ልጆቻቸውም የፈለጉትን ነገር የመምረጥ ነፃነት እንዳላቸው ይገነዘባሉ። ስለዚህ ለልጆቻቸው ‘እንዲህ አድርግ’ ወይም ‘አታድርግ’ የሚል ደንብ በማውጣት ብቻ አይወሰኑም፤ በኋላ ላይ አድገው በራሳቸው ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የሚችሉ በሳል አዋቂዎች እንዲሆኑ መርዳት ስለሚፈልጉ ከእያንዳንዱ ደንብ በስተ ጀርባ ያለውን ምክንያት ለማስረዳት ጥረት ያደርጋሉ።—ዘዳግም 6:6, 7፤ ቆላስይስ 3:21
ይህ ጥቅስ “ልጅን እንደ ተፈጥሮው አሠልጥነው” ወይም ‘ተፈጥሯዊ ዝንባሌውን ተከትለህ አሠልጥነው’ ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል ሐሳብ የሚሰጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አሉ። እንዲህ ያለው አተረጓጎም የሚያስኬድ ይመስል ይሆናል፤ ሆኖም “ሊሄድበት በሚገባው መንገድ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ አገላለጽ፣ ጥሩና ጽድቅ የሆነውን የሕይወት ጎዳና የሚያመለክት መሆን አለበት። የምሳሌ መጽሐፍ አንድ ሰው ሊሄድባቸው የሚችላቸውን ሁለት ጎዳናዎች ለይቶ ይጠቅሳል። አንደኛው ‘የጥሩ ሰዎች መንገድ፣’ ‘የጥበብ መንገድ’ እና “ትክክለኛው መንገድ” ተብሎ ተጠርቷል። (ምሳሌ 2:20፤ 4:11፤ 23:19) ሌላኛው ደግሞ ‘የክፉዎች መንገድ፣’ “የሞኝ መንገድ” እና ‘የተሳሳተ መንገድ’ ተብሏል። (ምሳሌ 4:14፤ 12:15፤ 16:29) በመሆኑም ልጅ ‘ሊሄድበት የሚገባው’ መንገድ የተባለው “ትክክለኛው መንገድ” መሆን አለበት፤ ይህም የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው የሕይወት መንገድ ነው።—መዝሙር 119:105
“በሚያረጅበት ጊዜም እንኳ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።” ወላጆች ልጃቸውን በአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ኮትኩተው የሚያሳድጉት ከሆነ በአብዛኛው ሕይወቱን በሙሉ ከትክክለኛው ጎዳና አይወጣም። ይህ ሲባል ግን ተገቢውን ሥልጠና ያገኘ ልጅ ሁሉ፣ ከትክክለኛው ጎዳና “ፈቀቅ አይልም” ወይም የአምላክን ሕጎች አይተውም ማለት አይደለም። ለምሳሌ አንድ ሰው መጥፎ ማድረግን ከሚያበረታቱ ሰዎች ጋር ከዋለ “ቀናውን ጎዳና” ሊተውና መጥፎ ነገር ማድረግ ሊጀምር ይችላል። (ምሳሌ 2:12-16፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) ያም ቢሆን ወላጆች፣ ልጆቻቸው የአምላክን መሥፈርቶች እንዲከተሉ የሚያሠለጥኗቸው ከሆነ ስኬታማ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል አጋጣሚ እየሰጧቸው ነው።—ምሳሌ 2:1, 11
የምሳሌ 22:6 አውድ
ምሳሌ ምዕራፍ 22 ስለተለያዩ የሕይወት እውነታዎች የአምላክን ጥበብ የሚያንጸባርቁ አጫጭር አባባሎችን ይዟል። እነዚህ አባባሎች በይሖዋ a ዘንድ መልካም ስም ማትረፍ ያለውን ዋጋ ያጎላሉ፤ እንዲህ ያለ ስም ማትረፍ የሚቻለውም ትሑት፣ ለጋስና ታታሪ በመሆን ነው። (ምሳሌ 22:1, 4, 9, 29) ከዚህ በተለየ መልኩ ደግሞ የአምላክን መሥፈርቶች ችላ የሚሉና በድሆች ላይ ግፍ የሚፈጽሙ ሰዎች መዘዙን እንደሚቀበሉ የሚያሳዩ ጥቅሶች አሉ።—ምሳሌ 22:8, 16, 22-27
እርግጥ ነው፣ በምሳሌ ምዕራፍ 22 ላይ የሚገኙት አብዛኞቹ ጥቅሶች ስለ ልጅ አስተዳደግ የሚናገሩ አይደሉም፤ ይሁንና የአምላክን ሞገስና እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘውን የሕይወት ጎዳና ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። (ምሳሌ 22:17-19) ለልጆቻቸው ከሁሉ የተሻለውን ሕይወት የሚመኙ ወላጆች በዚህ የሕይወት ጎዳና ላይ እንዲሄዱ ልጆቻቸውን ያሠለጥኗቸዋል።—ኤፌሶን 6:1-3
የምሳሌ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።