የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ሮም 12:2—“በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ”
“ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።”—ሮም 12:2 አዲስ ዓለም ትርጉም
“መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።”—ሮም 12:2 አዲሱ መደበኛ ትርጉም
የሮም 12:2 ትርጉም
አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች፣ ከመጥፎ ተጽዕኖዎች መራቅ ብቻ ሳይሆን ስብዕናቸውን መቀየርም አለባቸው። አምላክ እንዲህ ያለ ለውጥ እንዲያደርጉ አያስገድዳቸውም፤ ለውጥ የሚያደርጉት እሱን ስለሚወዱት እንዲሁም መመሪያዎቹ ደግነት የሚንጸባረቅባቸው፣ ምክንያታዊና ጠቃሚ እንደሆኑ ስለሚረዱ ነው።—ኢሳይያስ 48:17
“ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ።” እዚህ ላይ “ይህ ሥርዓት” የሚለው አገላለጽ፣ በዓለም ላይ ያለውን የሰው ልጅ ማኅበረሰብ እንዲሁም የሚከተላቸውን መሥፈርቶች፣ ልማዶችና የአኗኗር ዘይቤ ያመለክታል፤ ይህ ሥርዓት በአምላክ መሥፈርቶች ወይም አስተሳሰብ አይመራም። (1 ዮሐንስ 2:15-17) የሰዎችን ባሕርይ ወይም ስብዕና ለመቅረጽ የማያቋርጥ ግፊት ያሳድራል። አንድ ሰው አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ ከፈለገ የዓለምን ተጽዕኖ መቋቋም ይኖርበታል፤ ይህ ካልሆነ ግን ግለሰቡ ራሱን የሚጎዱና አምላክን የሚያሳዝኑ ልማዶችን ያዳብራል።—ኤፌሶን 2:1-3፤ 4:17-19
“አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።” አንድ ሰው በውስጣዊ ማንነቱ ማለትም በአስተሳሰቡና በስሜቱ ላይ ለውጥ ማድረግም አለበት። ጥቅሱ ላይ “ተለወጡ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል፣ ለውጡ ምን ያህል ስፋት እንደሚኖረው ይጠቁማል፤ ቃሉ አባጨጓሬ ወደ ቢራቢሮ ሲቀየር የሚያደርገውን ዓይነት ለውጥ ያመለክታል። አምላክን የሚያመልኩ ሰዎች ‘አዲስ ስብዕና’ መልበስ ይኖርባቸዋል።—ኤፌሶን 4:23, 24፤ ቆላስይስ 3:9, 10
‘ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ አረጋግጡ።’ አምላክ እሱን የሚያመልኩት ሰዎች ስለሚያምኑበት ነገር እርግጠኞች እንዲሆኑ ይፈልጋል። ይህን ማድረግ የሚቻለው የአምላክን ቃል በማጥናት፣ ቃሉን ተግባራዊ በማድረግና የአምላክን መሥፈርቶች መከተል የሚያስገኘውን ጥቅም በራስ ሕይወት በመመልከት ነው። በዚህ መንገድ፣ የአምላክ መሥፈርቶች ከሁሉ የተሻሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይቻላል።—መዝሙር 34:8
የሮም 12:2 አውድ
ሮም ምዕራፍ 12፣ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አምልኮ ማቅረብ ምን እንደሚያካትት ያብራራል። ለአምላክ የምናቀርበው አምልኮ መላ ሕይወታችንን ይነካል፤ በጭፍን ወይም እንዲሁም በስሜት ብቻ ከማምለክ ይልቅ ‘የማሰብ ችሎታን’ መጠቀምንም ይጠይቃል። (ሮም 12:1, 3) በዚህ ምዕራፍ ላይ ጥሩ ባሕርያትን ማሳየት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ፣ ከሌሎች ጋር ተስማምተን መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነና በደል ሲደርስብን ምን ምላሽ መስጠት እንዳለብን ጠቃሚ ምክር እናገኛለን።—ሮም 12:9-21