የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ዘፍጥረት 1:26—‘ሰውን በመልካችን እንሥራ’
“ከዚያም አምላክ ‘ሰውን በመልካችን እንደ አምሳላችን እንሥራ፤ እሱም በባሕር ዓሣዎች፣ በሰማያት ላይ በሚበርሩ ፍጥረታት፣ በቤት እንስሳትና በምድር ሁሉ እንዲሁም በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑረው’ አለ።”—ዘፍጥረት 1:26 አዲስ ዓለም ትርጉም
“እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፣ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።”—ዘፍጥረት 1:26 የ1954 ትርጉም
የዘፍጥረት 1:26 ትርጉም
የሰው ልጆች የተፈጠሩት በአምላክ መልክ ነው፤ ይህም ሲባል እንደ ፍቅር፣ ርኅራኄና ፍትሕ ያሉትን የአምላክ ባሕርያት የማዳበርና የማንጸባረቅ ችሎታ አላቸው ማለት ነው። ከዚህ አንጻር የሰው ልጆች የአምላክን ባሕርያት ሲያሳዩ ብንመለከት የሚያስገርም አይደለም።
‘አምላክ “ሰውን በመልካችን እንሥራ” አለ።’ ይሖዋ አምላክ a ከማንም ወይም ከምንም በፊት መጀመሪያ የፈጠረው በኋላ ላይ ኢየሱስ የተባለውን ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ነው። “በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ” የተፈጠሩት በኢየሱስ አማካኝነት ነው። (ቆላስይስ 1:16) የኢየሱስ ባሕርይ ልክ እንደ ይሖዋ ነው፤ “እሱ የማይታየው አምላክ አምሳል” ነው። (ቆላስይስ 1:15) በዚህም የተነሳ አምላክ ‘ሰውን በመልካችን እንሥራ’ ሊል የሚችለው ለኢየሱስ ነው።
“በቤት እንስሳትና በምድር ሁሉ . . . ላይ ሥልጣን ይኑረው።” እንስሳት የተፈጠሩት በአምላክ መልክ አይደለም። ተፈጥሯቸው ስላልሆነ እንደ ፍቅር ያሉትን የሰው ልጆች ባሕርያት ማንጸባረቅ አይችሉም፤ ሕሊናም የላቸውም። ሆኖም አምላክ ፍጥረቱ ስለሆኑ የእንስሳት ደህንነት ያሳስበዋል። የሰው ልጅ በእንስሳት ላይ “ሥልጣን ይኑረው” ብሎ የደነገገው ለዚህ ነው፤ ይህ ቃል “ይግዛ” (የ1954 ትርጉም) ወይም “ያስተዳድር” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። በመሆኑም ይሖዋ፣ የሰው ልጆች እንስሳትን እንዲንከባከቡ በአደራ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። (መዝሙር 8:6-8፤ ምሳሌ 12:10) የሰው ልጆች የምድርም ሆነ በላይዋ ያሉት ሕይወት ያላቸው ነገሮች ጠባቂ እንዲሆኑ ይፈልጋል።
የዘፍጥረት 1:26 አውድ
የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች አጽናፈ ዓለም፣ ምድራችን እንዲሁም በምድር ላይ ያሉት ሕይወት ያላቸው ነገሮች ስለተፈጠሩበት መንገድ ጠቅለል ያለ መግለጫ ይሰጡናል። ይሖዋ የፈጠራቸው ነገሮች ሁሉ በጣም አስደናቂ ናቸው፤ ሆኖም ምድር ላይ ከፈጠራቸው ነገሮች ሁሉ ቁንጮው የሰው ልጅ ነው ሊባል ይችላል። አምላክ የፍጥረት ሥራውን ሲያበቃ “የሠራውን እያንዳንዱን ነገር ተመለከተ፤ እነሆ፣ እጅግ መልካም ነበር!”—ዘፍጥረት 1:31
በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን ስለ ፍጥረት የሚገልጽ ታሪክ ማወቅ ከፈለግክ ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።
ሰዎች ስለ ዘፍጥረት 1:26 ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት
የተሳሳተ አመለካከት፦ የሰው ልጆች አምላክን የሚመስሉት በአካላዊ ገጽታቸው ነው።
እውነታው፦ “አምላክ መንፈስ ነው”፤ በመሆኑም የሚኖረው እኛ ከምናውቀው ግዑዙ አጽናፈ ዓለም ውጪ ነው። (ዮሐንስ 4:24) እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ፊት፣ እጅ፣ ልብ ወዘተ የሚናገርበት ጊዜ አለ፤ ሆኖም እነዚህን ዘይቤያዊ አገላለጾች የሚጠቀመው እኛን የሰው ልጆችን በሚገባን ቋንቋ ስለ አምላክ ለማስረዳት ነው።—ዘፀአት 15:6፤ 1 ጴጥሮስ 3:12
የተሳሳተ አመለካከት፦ ዘፍጥረት 1:26 ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደሆነ ያሳያል።
እውነታው፦ አምላክና ኢየሱስ የጠበቀ የአባትና የልጅ ዝምድና አላቸው፤ ሆኖም ኢየሱስ አምላክ ራሱ አይደለም። ኢየሱስ፣ አምላክ ከእሱ እንደሚበልጥ አስተምሯል። (ዮሐንስ 14:28) ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት፤ ወይም “ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
የዘፍጥረት መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።