ሰማይ ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ሰማይ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ይኸውም፦ (1) ግዑዙን ሰማይ፣ (2) መንፈሳዊውን ዓለም (3) ከፍ ያለ ወይም የላቀ ቦታን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ቃሉ በተጠቀሰበት ቦታ ላይ የትኛውን ትርጉም እንደሚያስተላልፍ ከአውዱ መረዳት ይቻላል። a
ግዑዙ ሰማይ። “ሰማያት” የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ ነፋስ የሚነፍስበትን፣ ወፎች የሚበሩበትን፣ ደመና ወደ ዝናብና በረዶ የሚቀየርበትን እንዲሁም መብረቅ የሚያበራበትን የምድርን ከባቢ አየር ያመለክታል። (መዝሙር 78:26፤ ምሳሌ 30:19፤ ኢሳይያስ 55:10፤ ሉቃስ 17:24) በተጨማሪም ‘ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት’ የሚገኙበትን ሕዋ ሊያመለክት ይችላል።—ዘዳግም 4:19፤ ዘፍጥረት 1:1
መንፈሳዊው ዓለም። “ሰማይ” የሚለው ቃል መንፈሳዊውን ሰማይ ማለትም ከግዑዙ ጽንፈ ዓለም ውጪ ያለውን መንፈሳዊ ዓለምም ያመለክታል። (1 ነገሥት 8:27፤ ዮሐንስ 6:38) በዚህ መንፈሳዊ ሰማይ ውስጥ የሚገኙት “መንፈስ” የሆነው ይሖዋ አምላክ እንዲሁም የእሱ መንፈሳዊ ፍጥረታት የሆኑት መላእክት ናቸው። (ዮሐንስ 4:24፤ ማቴዎስ 24:36) አንዳንድ ቦታዎች ላይ “ሰማያት” የሚለው አገላለጽ ‘የቅዱሳንን ጉባኤ’ ማለትም ታማኝ መላእክትን ያመለክታል።—መዝሙር 89:5-7
መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ‘የመኖሪያ ቦታ’ የሆነውን የመንፈሳዊውን ዓለም የተወሰነ ክፍል ለማመልከትም “ሰማያት” የሚለውን ቃል ይጠቀማል። (1 ነገሥት 8:43, 49፤ ዕብራውያን 9:24፤ ራእይ 13:6) ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ እንደሚወረወሩ ተናግሯል፤ ይህ ማለት ዳግመኛ በይሖዋ ፊት መቅረብ አይችሉም ማለት ነው። ሆኖም አሁንም የሚኖሩት በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ነው።—ራእይ 12:7-9, 12
ከፍ ያለ ወይም የላቀ ቦታ። ቅዱሳን መጻሕፍት “ሰማይ” የሚለውን ቃል በተለይ ሥልጣን ካላቸው አካላት ጋር በተያያዘ ከፍ ያለ ቦታን ለማመልከት ይጠቀሙበታል። ቃሉ የሚከተሉት አካላት ያላቸውን ቦታ ሊያመለክት ይችላል፦
ሁሉን ቻይና ሉዓላዊ ገዥ የሆነው ይሖዋ አምላክ።—2 ዜና መዋዕል 32:20፤ ሉቃስ 15:21
ሰብዓዊ መንግሥታትን በማጥፋት የሚገዛው የአምላክ መንግሥት። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መንግሥት “አዲስ ሰማያት” በማለት ይጠራዋል።—ኢሳይያስ 65:17፤ 66:22፤ 2 ጴጥሮስ 3:13 b
ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች።—ኤፌሶን 2:6
ራሳቸውን በተገዢዎቻቸው ላይ ከፍ ከፍ የሚያደርጉት ሰብዓዊ መንግሥታት።—ኢሳይያስ 14:12-14፤ ዳንኤል 4:20-22፤ 2 ጴጥሮስ 3:7
በአሁኑ ጊዜ ዓለምን እየገዙ ያሉት ክፉ መናፍስት።—ኤፌሶን 6:12፤ 1 ዮሐንስ 5:19
ሰማይ ምን ዓይነት ቦታ ነው?
መንፈሳዊው ዓለም በእንቅስቃሴ የተሞላ ነው። ‘የይሖዋን ቃል የሚፈጽሙ’ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት በሰማይ ላይ ይገኛሉ።—መዝሙር 103:20, 21፤ ዳንኤል 7:10
መጽሐፍ ቅዱስ ሰማይ በጣም ብሩህ እንደሆነ ይገልጻል። (1 ጢሞቴዎስ 6:15, 16) ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለ ሰማይ በተመለከተው ራእይ ላይ “ደማቅ ብርሃን” እንዳየ የገለጸ ሲሆን ዳንኤል ደግሞ በሰማይ ላይ “የእሳት ጅረት” በራእይ ተመልክቷል። (ሕዝቅኤል 1:26-28፤ ዳንኤል 7:9, 10) ሰማይ ቅዱስ ወይም ንጹሕ እንዲሁም ውብ ነው።—መዝሙር 96:6፤ ኢሳይያስ 63:15፤ ራእይ 4:2, 3
በጥቅሉ ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ ሰማይን የሚገልጽበት መንገድ በጣም አስደናቂ ነው። (ሕዝቅኤል 43:2, 3) ሆኖም የሰው ልጆች መንፈሳዊውን ዓለም ማየት ስለማይችሉ ስለ ሰማይ ሙሉ በሙሉ መረዳት አይችሉም።
a “ሰማይ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ከፍ ያለ” ወይም “ላቅ ያለ” የሚል ትርጉም ካለው ሥርወ ቃል የመጣ ነው። (ምሳሌ 25:3) ዘ ኒው ብራውን፣ ድራይቨር ኤንድ ብሪግስ ሂብሪው ኤንድ ኢንግሊሽ ሌክሲከን ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት ገጽ 1029ን ተመልከት።
b በማክሊንቶክና በስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ ኢሳይያስ 65:17 ላይ የተጠቀሱት አዲስ ሰማያት “አዲስ መስተዳድርን፣ አዲስ መንግሥትን” እንደሚያመለክቱ ይናገራል።—ጥራዝ 4 ገጽ 122