“ሰባት ቀሳፊ ኃጢአቶች” አሉ?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ “ሰባት ቀሳፊ ኃጢአቶች” ተብለው የተሰየሙ የኃጢአት ድርጊቶችን ለይቶ አይጠቅስም። ሆኖም አንድ ሰው ከባድ ኃጢአቶችን የሚፈጽም ከሆነ መዳን እንደማያገኝ ያስተምራል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ፆታ ብልግና፣ ጣዖት አምልኮ፣ መናፍስታዊ ድርጊት፣ በቁጣ መገንፈል እንዲሁም ስካር የመሳሰሉትን ከባድ ኃጢአቶች “የሥጋ ሥራዎች” በማለት ይጠራቸዋል። ከዚያም በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙ የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።”—ገላትያ 5:19-21 a
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘የሚጸየፋቸውን ሰባት ነገሮች’ ይዘረዝራል?
አዎ፣ ይዘረዝራል። ምሳሌ 6:16 እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም እሱ የሚጸየፋቸው ነገሮች ሰባት ናቸው።” ሆኖም በምሳሌ 6:17-19 ላይ የሚገኘው የኃጢአቶች ዝርዝር ሁሉንም ኃጢአቶች ያካተተ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከአስተሳሰብ፣ ከንግግር እንዲሁም ከድርጊት ጋር የተያያዙትን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ኃጢአቶች የሚወክሉ ክፍሎችን የያዘ ነው። b
“ቀሳፊ ኃጢአት” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል?
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች 1 ዮሐንስ 5:16 ላይ ይህንን አገላለጽ ተጠቅመውበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ዘ ኒው አሜሪካን ባይብል “ቀሳፊ ኃጢአት አለ” ይላል። እዚህ ጥቅስ ላይ “ቀሳፊ ኃጢአት” ተብሎ የተተረጎመው አገላለጽ “ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ታዲያ “ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት” እና “ለሞት የማያበቃ ኃጢአት” ልዩነታቸው ምንድን ነው?—1 ዮሐንስ 5:16
መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ዓይነት ኃጢአት ሞት እንደሚያስከትል በግልጽ ይናገራል። ሆኖም በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ከኃጢአትና ከሞት መዳን እንችላለን። (ሮም 5:12፤ 6:23) በመሆኑም “ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት” የሚባለው የክርስቶስ ቤዛ ምሕረት የማያስገኝለት ዓይነት ኃጢአት ነው። እንዲህ ዓይነቱን ኃጢአት የሚፈጽም ሰው፣ ሆነ ብሎ የኃጢአት ጎዳና የሚከተል ሲሆን አመለካከቱንም ሆነ ድርጊቱን ለመቀየር ፈቃደኛ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን ኃጢአት ‘ይቅር የማይባል ኃጢአት’ በማለትም ይጠራዋል።—ማቴዎስ 12:31፤ ሉቃስ 12:10
a በገላትያ 5:19-21 ላይ የሚገኘው የ15 ከባድ ኃጢአቶች ዝርዝር ሁሉንም ኃጢአቶች አካትቶ የያዘ አይደለም፤ ምክንያቱም ጥቅሱ እነዚህን ኃጢአቶች ከዘረዘረ በኋላ “እነዚህን የመሳሰሉ” ይላል። ስለሆነም አንባቢው የማስተዋል ችሎታውን ተጠቅሞ እዚህ ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱ ሆኖም“እነዚህን የመሳሰሉ” ሊባሉ የሚችሉ ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ መረዳት ይጠበቅበታል።